አልኮል ለጤናችን ጎጂ እና ጠቃሚ የሚሆነው መቼ ነው?
ጤናማ የአልኮል አጠቃቀም ማለትስ ምንድን ነው?
እውን ሰውነታችን አልኮል ያስፈልገዋል?
አልኮል ለጤናችን ጎጂ እና ጠቃሚ የሚሆነው መቼ ነው?
የሰው ልጅ አልኮልን መጠቀም ከጀመረ ዘመናትን ያስቆጠረ ሲሆን አመራረቱ እና አጠቃቀሙ በየጊዜው መልኩን እየቀየረ መጥቷል፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት አልኮል መጠቀም ከ200 በላይ ለሆኑ ህመሞች የሚዳርግ ሲሆን በዚያው ልክ ደግሞ አልኮል ለሰውነታችን አስፈላጊ እና ጠቃሚ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ይወጣሉ፡፡
ዩሮ ኒውስ በጤና አምዱ በሰራው ዘገባ አልኮል መጠቀም ሊያመጣቸው ስለሚችላቸው ጉዳቶች፣ ለሰውነት አስፈላጊ ይሆናል ስለሚባለው የአልኮል መጠን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የጤና ተመራማሪዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
በቪክቶሪያ ዩንቨርሲቲ የንጥረ ነገሮች አጠቃቀም ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ቲሞቲ ናይሚ እንዳሉት ከአልኮል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለሰው ልጅ ጤና ጠቃሚው ነገር ብዙ አለመጠጣት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የአልኮል መጠን በሰውነታችን ውስጥ በበዛ ቁጥር የተለያዩ ህዋሶች እንዲሞቱ እና እንዳያገግሙ በማድረግ ለተለያዩ የካንሰር አይነት ህመሞች እንደሚዳርግ ተገልጿል፡፡
እንደ ዶክተር ቲሞቲ አስተያየት ከሆነ ዝቅተኛ መጠን የአልኮል ተጠቃሚዎች የበለጠ እና የተሻለ ጤና እንዳላቸውም አክለዋል፡፡
አልኮል በተለይም ለጉበት፣ ጉሮሮ፣ አንጀት፣ የአፍ ውስጥ እና ለጡት ካንሰር ህመሞች እንደሚዳርግም ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
አልኮል መጠቀም ምንም አይነት ጥቅም የለውም? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም በቀን ውስጥ ወንዶች ሁለት ሴቶች ደግሞ ቢበዛ አንድ አልኮል ቢጠጡ ይመከራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ታዋቂው አሜሪካዊ የቀዶ ጥገና ዶክተር ቪቬክ መርቲ በበኩላቸው ሶዳ እና ጋዝ የተቀላቀለባቸው የአልኮል መጠጦች ለካንሰር ህመሞች የበለጠ እንደሚያጋልጡ ገልጸዋል፡፡
ከካንሰር እና ተያያዥ ለሆኑ ጽኑ ህመሞች ራስን ለመጠበቅ ራስን ከአልኮል መጠጥ መጠበቅ ዋነኛው ነገር እንደሆነም ዶክተር መርቲ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በአልኮል ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ለጤና ተስማሚ ወይም የተመጠነ አልኮል መጠጣት ለጤና ተስማሚ መሆናቸውን የሚያሳዩ ጥናቶች እንዳልተደረጉም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡