የአሜሪካው ዩኤስኤአይዲ ድጋፍ ማቋረጡን ተከትሎ ከ8 ሺህ በላይ እናቶች ከወሊድ ጋር በተገናኘ በሽታ ሊሞቱ እንደሚችሉ ተነገረ
በመላው አፍሪካ እና በሌሎች የአለም ክፍሎች ከተቋሙ የመድሀኒት እና የምግብ ድጋፍ የሚደርግላቸው ሰዎች ህይወት አደጋ ላይ ይገኛል ተብሏል
ከዚህ ባለፈም የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም መቋረጥ በርካታ ህጻናትን ደህንንት ስጋት ላይ ጥሏል
ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በመሆን የአሜሪካ ግዙፉ የእርዳታ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ እንዲዘጋ መወሰናቸውን ተከትሎ አዳዲስ የስጋት መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡
የተቋሙ መዘጋት የህይወት አድን መድሀኒቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ሌሎችም መሰረታዊ ድጋፎች ስርጭት ላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ከድርጅቱ ጋር በርካታ ፕሮጀክቶችን በጋራ የሚሰሩ የእርዳታ ድርጅቶች እና ተቋማት ቢሯቸውን ለመዝጋት እና ሰራተኞቻቸውን ለማሰናበት ተገደዋል፡፡
በዋናነት በእርዳታ ድርጅቱ ድጋፍ ከቆሙ 342 አለም አቀፍ የልማት እና እርዳታ ድርጅቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሊያቆሙ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም የቤተሰብ ምጣኔ፣ የበሽታ መከላከል እና ርሀብ እንዲሁም የትምህርት ተደራሽነት ላይ የድጋፉ መቋረጥ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ተነግሯል፡፡
በ2023 አመት ብቻ ከ40 ቢሊየን ዶላር በላይ እርዳታ ያደረገው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ መቋረጥ የሰዎችን ሞት ህይወት ሊያስከትል እንደሚችል ያስነበበው ዘ ጋርዲያን ነው፡፡
ከ8 ሺህ በላይ ሴቶች እና ልጃገረዶች በእርግዝና እና በወሊድ ምክንያት በሚከሰቱ የጤና እክሎች በቅድሚያ የሞት አደጋ ከተጋረጠባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በዩጋንዳ የወባ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ፕሮጀክቶች በመቋረጣቸው የበሽታው ስርጭት ሊያንሰራራ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እጅግ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ባለበት በሱዳን፣ እንዲሁም በቅርቡ በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል የተባባሰ ግጭት የሚካሄዱባት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚያጋጥሙ ወሳኝ የነፍስ አደን መድሀኒቶች እጥረት ስጋትን ጭረዋል፡፡
ዘጋርዲያን ያነጋገራቸው የዩኤስኤአይዲ ሰራተኞች ለሁለቱ ሀገራት በዚህ ወር ወደነዚህ ሀገራት መላክ የነበረባቸው መሰረታዊ መድሀኒቶች ከመጋዘን እንዳይወጡ ታግደዋል፤ ይህም በቅርብ በቀናት ውስጥ መድሀኒቶቹ ባለመድረሳቸው ሰዎች መሞታቸውን ልንሰማ እንችላለን ብለዋል፡፡
በመላው አፍሪካ፣ በእስያ በላቲን አሜሪካ እና ሌሎቸም የአለም ክፍሎች በዩኤስኤአይዲ ድጋፍ አማካኝነት የሚከናወኑ የትምህርት ምገባ ፕሮግራሞች መቋረጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ ድህነት እና የሰላም ማደፍረስንም ሊያባብስው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡