አሜሪካ በሄይቲ ሰላም ለማስከበር ለተሰማሩ የጸጥታ ሀይሎች የምታደርገውን ድጋፍ አቋረጠች
በኬኒያ ፖሊስ የሚመራው የሰላም አስከባሪ ሀይል የአሜሪካ ድጋፍ ከመቋረጡም በፊት በበጀት እጥረት ችግር ላይ ይገኛል
በአሁኑ ወቅት በወሮበላ ቡድኖቹ የሚመለመሉ ህጻናት ቁጥር በ70 በመቶ ማሻቀቡን ሪፖርቶች አመላክተዋል
የተባሩት መንግስታት ድርጅት በሄይቲ ሰላም ለማስከበር ለተሰማራው ልዑክ አሜሪካ የምታደርገውን ድጋፍ ማቋረጧን አስታወቀ፡፡
ባለፈው አመት የተጀመረው እና በገንዘብ እጥረት እየታገለ የሚገኝው በኬንያ ፖሊሶች የሚመራው ተልዕኮን በገንዘብ በመደገፍ ትልቁን አስተዋጽኦ የምታበረክተው አሜሪካ ናት፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች “ከአሜሪካ በተጻፈ ደብዳቤ የገንዘብ ድጋፉ መቋረጡ ተገልጾልናል፤ ይህ ቀድሞም ቢሆን በገንዘብ እና ትጥቅ እጥረት እየተፈተነ የሚገኘውን ተልዕኮ ተጨማሪ ችግር የሚፈጥርበት ነው” ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የሄይቲ ባለስልጣናት የሀገሪቱን በርካታ ግዛቶች ከተቆጣጠሩት የወንጀለኛ ቡድኖች ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ ለመደገፍ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የፖሊስ አባላት እንዲሰማሩ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
ይህ የሰላም አስከባሪ ሀይል 2500 አባላት እንደሚኖሩት ቢነገርም እስካሁን ወደ ስፍራው ያቀኑ ፖሊስ አባላት ቁጥር 800 ብቻ ናቸው፡፡
በገንዘብ ደረጃ ለተልዕኮው 63 ሚሊየን ዶላር ከምታዋጣው ካናዳ ቀጥሎ አሜሪካ 15 ሚሊየን ዶላር በመስጠት ሁለተኛ ናት፡፡
ዋሽንግተን በቀጥታ ለተመድ ከምታደርገው ድጋፍ ባለፈ 300 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች እና ተሸከርካሪዎችን ድጋፍ አድርጋለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ሀገራት የተለያዩ ድጋፎችን ለ90 ቀናት ማቋረጣቸውን ተከትሎ የሄይቲ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ጨምሮ ሌሎች በዋሽግተን ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ የሚደረግላቸው አለምአቀፋዊ ተልዕኮዎች በስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባሳለፍነው ጥቅምት መጨረሻ ላይ ባደረጉት ንግግር አለም አቀፉ ማህበረሰቡ ለሄይቲ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር ካልቻለ በቅርቡ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ሙሉለሙሉ በወሮበሎች የምትተዳደር ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ዋና ጸሀፊው አክለውም ለሰላም አስከባሪ ሀይሉ ተጨማሪ የሰው ሀይል እና በመሳሪያ ማደራጀት ካልተቻለ የመላ ሀገሪቷ እጣ ፈንታ በወሮበሎች እጅ መውደቅ የሚያፋጥን ስለመሆኑ አሳስበዋል፡፡
ዋና ከተማዋን ፖርት አዩ ዘፕሪንስን 80 በመቶ የተቆጣጠሩት የወሮበላ ቡድኖች በሀገሪቱ የተፈጠረውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደ አጋጣሚ በመጠቀም 70 በመቶ ህጻናትን መመልመላቸውን ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡