በሱዳን ብሉናይል ግዛት በተፈጠረ ግጭት ከ65 በላይ ሰዎች ተገደሉ
በብሉናይል ግዛት በተከሰተው የጎሳ ግጭት ከሟቾች በተጨማሪ ከ200 በላይ ሰዎች ቆስለዋል
ግጭቱ በርቲ እና ሀውሳ በተባሉ ጎሳዎች መካከል መከሰቱ ተገልጿል
በሱዳን ብሉናይል ግዛት በተፈጠረ ግጭት ከ65 በላይ ሰዎች ተገደሉ፡፡
በሱዳን ብሉናይል ተብሎ በሚጠራው ግዛት በበርቲ እና ሀውሳ ጎሳዎች መበካከል በተፈጠረ የጎሳ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ65 በላይ የደረሰ ሲሆን ከ200 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከሰዎች መጎዳት ባለፈም ከ16 በላይ የንግድ ሱቆች በዚሁ የጎሳ ግጭት ምክንያት ሲወድሙ ሌሎች መሰረተ ልማቶችም እንደወደሙ ተገልጿል፡፡
ብሉናይል ግዛት ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች ያለ የሀገሪቱ ክፍል ሲሆን ከዚህ በፊት መሰል አደጋዎች ይከሰቱበታል፡፡
በደቡብ ሱዳንም ተመሳሳይ የጎሳ ግጭት ተከስቶ 65 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከ150 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለው ነበር፡፡
የሱዳን ጤና ሚኒስትር ጀማል ናስር ኤል ሳያድ እንዳሉት ባሳለፍነው ቅዳሜ በተከሰተው በዚህ አደጋ የተጎዱ ሰዎች አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ዛሬ ጠዋት ላይ በብሉ ናይል ግዛት መቀመጫ ዳማዚን ከተማ ላይ በተከሰተው እና በቀጠለው በዚሁ አደጋ ከ16 በላይ የንግድ መገበያያዎች መውደማቸው ተገልጿል፡፡
ግጭቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን የሟቾች እና ተጎጂዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የግዛቲቱ ባለስልጣናት የተናገሩ ሲሆን ተጨማሪ ወታደሮች እንዲገቡላቸው ጠይቀዋል፡፡
በአል ሩሳሪስ ሆስፒታል ያለው የህክምና ቁሳቁሶች እያለቁ መሆናቸውን የተናገሩት ባለስልጣናቱ በግጭቱ ቆስለው ወደ ህክምና ተቋማት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ደግሞ እየጨመረ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የግዛቲት ባለስልጣናት በብሉ ናይል ዋና ዋና ከተሞች ለአንድ ወር የሚቆይ የሰዓት እላፊ ቢጥሉም በርካቶች አሁንም ግጭቱ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡