መንግስት “የትግራይ ክልል መሰረተ ልማትን መልሶ ለመገንባት” ከተመድ ጋር የ3ኛ ወገን ትግበራ ስምምነት ተፈራረመ
ስምምነቱ መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት እና የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎችን ለመርዳት ያለመ ነው
ህወሓት፤ ትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት የተፈረመው ስምምነት “አልገባኝም” ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት በህሓት ኃይሎች እና በፌደራል መንግስት መካከል በተፈጠረ ግጭት የወደመውን መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት ከተባበሩት መንግስታት ጋር የሶስተኛ ወገን ትግበራ ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በኩል መንግስትን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ በተመድ የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ (ዩኤንኦፒኤስ) በኩል ደግሞ ወ/ሮ ወርቅነሽ መኮንን ናቸው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ብሄራዊ የማገገሚያ መርሃ ግብሩ" የመሰረተ ልማት መልሶ የመገንባት፣ የአስፈላጊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማሻሻል እና የጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ለመርዳት ያለመ ነው ብሏል፡፡
"በትግራይ ያሉ ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ እና መንግስት ፕሮጀክቱን በራሱ መዋቅር ለማስፈጸም እስኪችል ድረስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ ፕሮጀክቱን በትግራይ ተግባራዊ ያደርጋል" ሲልም መግለጫው አክሏል።
ከመንግስት ጋር ስምምነቱን የተፈራረመው የተመድ የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ (ዩኤንኦፒኤስ)፤ ጦርነት በተጎዳው የሰሜኑ ክፍል እና ባብዛኛው በህወሐት ስር በሚገኘው የትግራይ ክልል የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ እንደሚገነባ መግለጹም ሚኒስተሩ አስታውቋል፡፡
ከጾታዊ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን የሚረዳበት ሌላው የፕሮግራሙ ክፍል በሌላ አካል የሚተገበር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ላይ ድርድር እየተካሄደ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
መንግስት በጦርነት የወደመው የትግራይ ክልልን መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት ይህን ይበል እንጂ፤ ጉዳዩ በህወሐት በኩል ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ፤ “ይህ ነገር ምን ማለት እንደሆነ እና እንዴት እንደሚሰራ አልገባኝም” ብለዋል፡፡
“መልስ ለማግኘት እየጮህኩ ነው!” ሲሉም ስምምነቱ ያልጠበቁትና የማይቀበሉት በሚመስል መልኩ ገልጸውታል፡፡
እንደረፈረንጆቹ በህዳር 2020 በመንግስት እና በህወሓት መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ብዙ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋሮች ቀደም ሲል ሲሰጡት የነበረን እርዳታ ቀንሰው እንደነበረ ይታወቃል።
መንግስት በሚያዝያ ወር የእርዳታ ወደ ትግራይ የመላክ ሂደት እንደገና በመፍቀድ እርዳታ የጫኑ መኪናዎች ወደ ክልሉ እንዲመለሱ መፍቀዱም ተከትሎ ወደ ትግራይ ሚገባው እርዳታ በእጅጉ የተሻሻለ መምጣ ይታወቃል።
ትግራይ አሁንም እንደ መብራት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን እና ባንክ ያሉ አስፈላጊ አገልግሎቶችን የሌሉበት እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ የሚገኙበት ክልል እንደሆነ የተመድ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባው የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በግጭት እና በአሰቃቂ ድርቅ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች 715 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እና ብድር ለመስጠት ባለፈው ወር መስማማቱ አይዘነጋም።