የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ተገለጸ
የዩንቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) በስራ ላይ ከታዩ አንድ ወር እንዳለፋቸው ተቋሙ ገልጿል
ትምህርት ሚንስቴር እና የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ተቋማት ስለ ጉዳዩ ከመናገር ተቆጥበዋል
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ተገለጸ።
ከሶስት ዓመት በፊት የደብረ ብርሀን ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) በቢሯቸው ከታዩ አንድ ወር አልፏቸዋል ተብሏል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዩንቨርሲቲው አስተዳድር አመራር አባል ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት "ፕሬዝዳንቱ ከመጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ በስራ ላይ አይተናቸው አናውቅም" ብለዋል።
"ፕሬዝዳንቱ ንጉስ ታደሰ ከተጠቀሰው ቀን አንስቶ የት እንደሄዱ እና መቼ እንደሚመለሱ አናውቅም" ሲሉም እኝህ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አመራር ነግረውናል።
ይሁንና ፕሬዝዳንቱ በቢሮ መታየት ካቆሙ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ባልታወቁ ሀይሎች መታገታቸውን ሰምተናል ሲሉም አክለዋል።
የሰማን ሸዋ ዞን ፖሊስ፣ ኮማንድ ፖስት፣ ትምህርት ሚንስቴር እና የደብረብረሀን ከተማ ፖሊስ ስለ ደብረ ብርሀን ዩንቨርስቲ ፕሬዝንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
እንዲሁም የፕሬዝዳንቱ ቤተሰብ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡን ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሼ አደራጃለሁ" የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ንጹሀን ዜጎች ከጥቃት እንዳልተጠበቁ እና ለተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጋለጣቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ ባወጧቸው ሪፖርቶች አስታውቀዋል።
አንዚህ ተቋማት ንጹሀን ዜጎች ለግድያ፣ ጅምላ እስር፣ እገታ፣ አስገድዶ መሰወር እና ሌሎች ጥቃቶች መጋለጣቸውንም በሪፖርቶቻቸው ላይ ጠቅሰዋል።