"ጂቡቲና ኬንያ ግብይት ለመፈጸም ዶላር አያስፈልጋቸውም" - ፕሬዝዳንት ሩቶ
የኬንያው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው ገንዘብ መገበያየት እንዲጀምሩ ጠይቀዋል
ሀገራቱ በገንዘባቸው ግብይት የሚፈጽሙበትን ስርአት የአፍሪ ኤግዚም ባንክ ማበጀቱ ተነግሯል
ኬንያ የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ ግብይት ሲፈጽሙ እና አገልግሎት ሲለዋወጡ በራሳቸው ገንዘብ ክፍያ መፈጸም እንዲጀምሩ ጠይቃለች።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በጂቡቲ ፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው “በዶላር ላይ ጥገኝነቱ ይብቃ” ያሉት።
“ከጂቡቲ እቃ ገዝተን በዶላር የምንከፍለው ለምንድን ነው? ለምን? ምንም ምክንያት የለም” ያሉት ፕሬዝዳንት ሩቶ፥ ጂቡቲም ሆነች ኬንያ የእርስ በርስ ግብይት ሲፈጽሙ የአሜሪካ ዶላር መጠቀም አያስፈልጋቸውም ብለዋል።
“እኛ የአሜሪካን ዶላር እየተቃወምን አይደለም፤ በነጻነት ግብይት መፈጸም ስለፈለግን እንጂ” ሲሉም አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንቱ “ዶላር የሚያስፈልገን ከአሜሪካ ጋር ለምናደርገው ግብይት ብቻ ነው” ማለታቸውንም ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ አስነብቧል።
በፈረንጆቹ 1993 የተቋቋመው የአፍሪ ኤክዚም ባንክ ግብይቱ በየሀገራቱ ገንዘብ እንዲከናወን የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም አውስተዋል።
ኬንያ በዚሁ ባንክ የተዋወቀውን የፓን አፍሪካ የክፍያ ስርአት ቀድማ ወደ ስራ እንደምታስገባም ነው ያረጋገጡት።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከዶላር ውጭ በገንዘባቸው ግብይት የሚፈጽሙበትን ዝርዝር ጉዳይ በጂቡቲ በተካሄደው 14ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ሳይመከርበት እንዳልቀረ ዘገባው ያመላክታል።
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ችግር ያለባቸው የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ የንግድ ትስስራቸውን ለማጠናከር የኬንያ ጅምር መልካም ውጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል።
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 90 በመቶ የዓለማችን የውጭ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በአሜሪካ ዶላር መከናወኑን የአለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም (አይኤምኤፍ) መረጃ ያሳያል።
በዓለማችን ከ6 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ንግድ በአሜሪካ ዶላር ቢካሄድም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ሆኖ መመዝገቡን ነው ተቋሙ ያስታወቀው።
ሀገራት በአሜሪካ ዶላር የሚያስቀምጡትን ተቀማጭ ሃብታቸውንም ወደ ሌላ ገንዘብ እየቀየሩ መሆናቸው ፥ ዶላር በዓለም ንግድ ላይ ያለው ድርሻ ከ20 ዓመት በኋላ ቅናሽ እንዲያሳይ አድርጎታል ነው የተባለው።
ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድን ጨምሮ የምዕራባውያን ጫና ያረፈባቸው ሀገራት ዶላርን በመተው በራሳቸው ገንዘብ መገበያየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
የአፍሪካ ሀገራትም ግብይት ለመፈጸም ዶላር ከመጠበቅ የሚላቀቁበትን አሰራር ከዘረጉ ቢሰነብቱም ወደ ስራ ለመግባት ግን ተቸግረዋል።