ደቡብ ኮሪያ ዲፕሲክ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቲክቶክ እያጋራ ነው ስትል ከሰሰች
ዲፕሲክን ያገደችው ሴኡል የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸውን በዲፕሲክ "ቻትቦት" ላይ እንዳያጋሩ አሳስባለች
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/273-172926-2a38e8b0-edde-11ef-9cb9-3360cc750412_700x400.jpg)
አሜሪካ፣ ጣሊያን እና አውስትራሊያ የቻይናውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያ ካገዱ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ
ደቡብ ኮሪያ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት ያገኘው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያ ዲፕሲክ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቲክቶክ እያጋራ ነው ስትል ከሰሰች።
የደቡብ ኮሪያ የመረጃ ጥበቃ ተቋም "ዲፕሲንክ ከቲክቶኩ ባይትዳንስ ጋር መረጃ እንደሚለዋወጥ አረጋግጠናል" ብሏል።
ዲፕሲክ ለሌላኛው የቻይና ኩባንያ ባይትዳንስ ምን ያህል የተጠቃሚዎችን መረጃ እንዳስተላለፈ ግን በዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘገባ ላይ አልተጠቀሰም።
ተቋሙ የዲፕሲክ ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸውን በመተግበሪያው "ቻትቦት" ላይ እንዳያጋሩ አሳስቧል።
ስኮርካርድ የተሰኘው የሳይበር ደህንነት ተቋም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያው ዲፕሲክ የተጠቃሚዎቹን ባህሪ እና የሚጠቀሙትን ስልክ ዝርዝር መረጃ ለባይትዳንስ ሳይልክ አልቀረም ብሏል።
ደቡብ ኮሪያ ከአራት ቀናት በፊት ዲፕሲክ መተግበሪያ ከአፕል እና ጎግል ስቶር ላይ እንዲነሳ ማድረጓ ይታወሳል።
ከዚህ ውሳኔ በፊት ግን ከ1 ሚሊየን በላይ የሀገሪቱ ዜጎች መተግበሪያውን አውርደውታል፤ በኮምፒውተሮች ላይ ይህንን መተግበሪያ የሚጠቀሙት ግን አሁንም አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ቀጥለዋል።
የቻይናው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያ "ዲፕሲክ" በ5 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ወጪ ነው የተሰራው።
መተግበሪያው እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ በቢሊየን ዶላሮች ወጪ ተደርጎባቸው የሰለጠኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች በክፍያ የሚሰጡትን አገልግሎት በነጻ ማቅረቡ በአጭር ጊዜ ከመላው አለም ተጠቃሚዎች እንዲጎርፉለት አድርጓል።
ባለፈው ጥር ወር የተዋወቀው መተግበሪያ ዝናው ቢናኝም እንደ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ አውስትራሊያ እና ቤልጂየም ያሉ ሀገራት የተጠቃሚዎች መረጃ አያያዙ አጠራጣሪ ነው በሚል አግደውታል።
የአሜሪካ የሳይበር ደህንነት ኩባንያም በቅርቡ ዲፕሲክ ከቲክቶክ ባለቤት ኩባንያ ባይትዳንስ ጋር መረጃ ይለዋወጣል የሚል ወቀሳ አቅርቦበት እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።
ተንታኞች የቻይና የስለላ ህግ መንግስት ከትኛውንም የቻይና ኩባንያ የሚፈልገውን መረጃ ማግኘት እንደሚችል ያስቀምጣል ይላሉ።
በቤጂንግ ያለው የባይትዳንስ ዋና ቢሮ የሚገኝበት ህንጻ በአለማቀፍ ባለሃብቶች የሚተዳደር ቢሆንም ህጉ ለግል ኩባንያዎችም ተመሳሳይ ይዘት ያለውና መረጃዎችን ማጋራትን የሚያስገድድ መሆኑንም ያብራራሉ።
አሜሪካ በቲክቶክ ላይ እገዳ ስትጥል ካነሳቻቸው መሰረታዊ ምክንያቶች አንዱ የተጠቃሚዎች መረጃ በቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ እጅ በቀላሉ ይገባል የሚለው እንደነበር የሚታወስ ነው።