ህንድ ሁለት ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ልትገነባ ነው
በኒዩክሌር የሚሰሩትን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ለመገንባት 5.4 ቢሊየን ዶላር ወጪ ይደረጋል ተብሏል
ህንድ ጎርቤቷ ቻይና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ያላትን ተጽዕኖ ለመግታት የባህር ሃይሏን በማጠናከር ላይ ትገኛለች
ህንድ ሁለት ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት የቀረበውን እቅድ አጸደቀች።
ኒው ደልሂ በኒዩክሌር የሚሰሩትን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ለመገንባት 450 ቢሊየን ሩፒ ወይንም 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደምታደርግም ነው ሬውተርስ የሀገሪቱን የደህንነት ምንጮች ጠቅሶ ያስነበበው።
ህንድ ጎረቤቷ ቻይና በህንድ ውቅያኖስ ክልል ተጽዕኖዋ እየጎላ መሄድ እንደሚያሳስባት ደጋግማ ገልጻለች።
በዚህም የባህር ሃይሏን በማጠናከርና በሀገር ውስጥ የጦር መሳሪያዎችን የማምረት አቅሟን በማሳደግ ላይ ተጠምዳለች ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ካቢኔም የሀገሪቱ ባህር ሃይል ካቀረበው ስድስት በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ ዘመናዊ ባህርሰርጓጅ መርኮቦች ይገንቡ ጥያቄ ውስጥ የሁለቱን ማጽደቁ ነው የተገለጸው።
በባህር ውስጥ ከእይታ ተሰውረው የኒዩክሌር መሳሪያዎችን ጭምር መተኮስ ይችላሉ የተባሉት ባህርሰርጓጅ መርከቦች ግንባታ መቼ ተጠናቆ የባህር ሃይሉን እንደሚቀላቀሉ ግን አልታወቀም።
በአለማችን ጠንካራ ባህር ሃይል ካላቸው ሀገራት በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ቻይና 12 በኒዩክሌር ሃይል የሚሰሩ ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ባለቤት መሆኗን የስታስቲካ መረጃ ያሳያል።
አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይና ብሪያንያም በኒዩክሌር የሚሰሩ ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ህንድም ሁለት ባህርሰርጓጅ መርከቦችን ከሩሲያ በሊዝ ተቀብላ ስትጠቀም የቆየች ሲሆን፥ ከመለሰች በኋላም ሌሎች መርከቦችን ለመውሰድ በንግግር ላይ ትገኛለች።
አዳዲሶቹ በራሷ አቅም የምትሰራቸው ሁለት ባህር ሰርጓክ መርከቦች በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ቪሳክሃፓትናም ወደብ ይገነባሉ ተብሏል።
ባህር ሰርጓጅ መርከቦቹ “አሪሃንት ክላስ” ከተባሉት መርከቦች የተለዩና የኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎችን ማስወንጨፍ የሚችሉ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
የህንድ እና ቻይና ግንኙነት በ2020 በሂማሊያ 24 ወታደሮች በተኩስ ልውውጥ ህይወታቸው ካለፈው በኋላ መሻከሩ ይታወሳል።