ዱባይ ከሱቆች እቃ ገዝተው የሚመጡ ሮቦቶችን እየሞከረች ነው
“ታላቦት” የተሰኙት ሮቦቶች ምግብና ሎሎች እቃዎችን ገዝተው ላዘዛቸው አካል እንዲያደርሱ ተደርጓል
ዱባይ በ2030 አሽከርካሪ አልባ የትራንስፖርት አማራጮችን 25 በመቶ ለማድረስ እቅድ አላት
የተባበሩት አረብ ኤምሬትሷ ዱባይ የሚላላኩ ሮቦቶችን በመሞከር ላይ ናት ተብሏል።
የዱባይ የመንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን እንዳስታወቀው፥ “ታላቦት” የተሰኙት ሮቦቶች ከሱቅ እና ሱፐርማርኬቶች እቃዎችን ገዝተው ለአዘዘው ሰው የሚያደርሱ ናቸው።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚጠቀሙትን ሮቦቶች እንቅስቃሴ በሞባይል ስልክ መከታተል ይቻላል።
ሮቦቶቹ በከተማዋ ቅንጡ ቤቶች በተገነባበት ሲድር የቪላ መንደር የሙከራ ተልኳቸውን ሲፈጽሙ ነበር ተብሏል።
በዚህም ሶስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ እቃን ገዝተው ወደሚፈለገው ስፍራ ለማድረስ ከ15 ደቂቃ ያነሰ ጊዜ ወስዶባቸዋል ብሏል ባለስልጣኑ።
ሮቦቶቹ የበካይ ጋዝ ልቀትን ከመከላከል ባሻገር ከሰዎች ንክኪ ነጻ የሆነና ዘመኑንን የዋጀ ፈጣን አገልግሎት ለማድረስ እንደሚያግዙ የዱባይ የቴክኖሎጂ መንደር (ሲልከን ኦሲስ) ዳይሬክተሩ ዶክተር ጁማ አል ማትሩሺ ተናግረዋል።
2023ትን “የዘላቂነት አመት” ብላ የሰየመችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከባካይ ጋዝ ልቀት ነጻ የሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በስፋት በመጠቀም ላይ ትገኛለች።
በፈረንጆቹ ህዳር ወር 2023 በምታዘጋጀው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤም (ኮፕ28) በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የደረሰችበትን ደረጃ ታሳያለች ተብሎ ይጠበቃል።
የንግድ ከተማዋ ዱባይም በሮቦት ቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ የሚያደርጓት ስራዎች መቀጠላቸው ተገልጿል።
ዱባይ በ2030 የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 25 ከመቶው ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ እንዲሆኑ አቅዳ እየሰራች ነው።
ምግብና መጠጦችን ጨምሮ የተለያዩ ትዕዛዞችን ተቀብለው ከሱቆችና ሱፐርማርኬቶች እቃዎችን ሸምተው ለባለቤቱ የሚያደርሱት “ታላቦት” ሮቦቶችም የዚሁ እቅዷ አካል ነው ተብሏል።
በ2020 የዱባይ ኤክስፖ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት እነዚህ ሮቦቶች ሙከራቸው እንደተጠናቀቀ በዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች ስራ እንደሚጀምሩ የዱባይ መንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል።