ሮቦቱ ከፍጥነት ገደብ በላይ በማሽከርከር የተከሰሰ ደንበኛውን ነጻ ለማውጣት ነው ፍርድ ቤት የሚቆመው
የዓለማችን የመጀመሪያው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጠበቃ ስራ ሊጀምር መሆኑ ተሰምቷል።
DoNotPay በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ የበለፀገው "ሮቦት ጠበቃ" ከደንበኛው ጋር ፍርድ ቤት በመቅረብ ነው ስራውን የሚጀምረው።
ይህ የሮቦት ሥርዓት ከፍጥነት ገደብ በላይ በማሽከርከር የተከሰሰ ደንበኛውን ነጻ ለማውጣት የሕግ ምክር ሊለግስ በቀጣዩ የካቲት ወር ፍርድ ቤት እንደሚቆም ዴይሊ ሜይል አስነብቧል፡፡
ተከሳሹ በፍርድ ቤት በሚኖረው ቆይታ የጠበቃውን ምክር ለመስማት የስማርት ስልክ መተግበሪያ እና የማዳመጫ መሳሪያ (ኤርፎን) እንደሚጠቀም ተገልጿል፡፡
በዚህም ሮቦት ጠበቃው በተከሳሹ ስማርት ስልክ ላይ በመሆን ከዓቃቤ ሕግ የሚቀርበውን ክስ እና አስተያየት በመስማት ደንበኛው በክርክሩ ወቅት ምን መመለስ እንዳለበት መመሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ሮቦቱ ይህን ማድረግ የሚያስችለውን አቅም ያገኘው ተጨባጭ የሕግ እውነታዎችን መሠረት አድርጎ በመሠልጠኑ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
የDoNotPay ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆሹዋ ብሮውደር በድርጅታቸው የበለፀገው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓት በፍርድ ቤት በሚያደርገው ክርክር ቢሸነፍ ተከሳሹ ሊደርስበት ለሚችለው ቅጣቶች ለመካስ ቃል ገብተዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ጥብቅና የሚቆምለትን ግለሰብ እና ችሎቱ የሚካሄድበትን ፍርድ ቤት ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
"ሮቦት ጠበቃ" ስራ ላይ የመዋሉን ጉዳይ ችግር ውስጥ ሊጥል የሚችለው ግን ፍርድ ቤቶች ለቴክኖሎጂዎች ያላቸው ምልከታ ነው።
በአሜሪካ በርካታ ፍርድ ቤቶች ተከሳሾች ጆሮ ላይ የሚደረጉና በብሉቱዝ የሚተሳሰሩ ማዳመጫዎችን መጠቀም ይከለክላሉ።
የDoNotPay ሮቦት ጠበቃም ከባለጉዳዩ ጋር የሚግባባው በቴክኖሎጂ እንደመሆኑ የፍርድ ቤቶችን ይሁንታ የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው ተብሏል።
ኩባንያው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ወይም በሮቦቶች ሊጀምራቸው ካሰባቸው 300 የክስ ጉዳዮች መካከል ሁለቱ ብቻ ተመርጠዋል።
የመጀመሪያው ሙከራም ከፍጥነት ገደብ በላይ በማሽከርከር ለተከሰሰ ግለሰብ ጠበቃ በመቆም ይጀመራል ተብሏል።