ፌስቡክ እና አፕልን ጨምሮ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከ50 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ቀንሰዋል
የአሜሪካው የኮምፒውተር አምራች ኩባንያ ዴል ሰራተኞቹን ለማሰናበት ማቀዱን አስታውቋል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው 6 ሺህ 650 ሰራተኞች በመቀነስ ነው የግዙፍ ኩባንያዎችን መሰል እርምጃ የሚቀላቀለው።
ዴል ከጠቅላላ ሰራተኞቹ 5 በመቶውን የሚያሰናብተው የኮምፒውተሮቹ ገበያ በመቀዛቀዙ መሆኑን ብሉምበርግ ዘግቧል።
የኩባንያው ምክትል ሊቀመንበር ጄፍ ክላርክ ጽፈውታል የተባለው የሰራተኞች ማሰናበቻ ደብዳቤ፥ የኮምፒውተር ሽያጭ መንኮታኮትን ያመላክታል።
የዴል የአክሲዮን ገበያም በ1 ነጥብ 1 በመቶ መውረዱ አሳሳቢ ስለመሆኑ ነው የተነገረው።
ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አለም የገጠማት ፈተና ተጽዕኖ እንዳደረሰባቸው በመግለጽ ከ50 ሺህ በላይ ሰታተኞችን ከስራ አሰናብተዋል።
ጎግል በጥር ወር 2023 ከ12 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ማሰናበቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ማይክሮሶፍትም ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞችን በመቀነስ የገጠመውን ችግር ለማቃለል ማሰቡን ማሳወቁ አይዘነጋም።
አማዞንም ከፍተኛውን የሰራተኛ ቅነሳ (18 ሺህ) ለማድረግ እቅድ መያዙን ይፋ ያደረገው በቅርቡ ነው።
የስዊድኑ የሙዚቃ ማሰራጫ ስፖቲፋይም ከ6 በመቶ በላይ ሰራተኞቹን በማሰናበት ወጪውን ለመቀነስ ይፋ ማድረጉን ሬውተርስ አስታውሷል።
የሰራተኞች ቅነሳውን በመጀመር ቀዳሚ የሆነው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ፌስቡክ በህዳር ወር 2022 ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ማሰናበቱ አይዘነጋም።
ትዊተር፣ አማዞን፣ ማይክሮሶፍት፣ አፕል እና ሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎችም ሰራተኞችን የመቀነስ ውሳኔ ማሳለፋቸው የሚታወስ ነው።