በትግራይ ጊዜያዊ መንግስት በአጭር ጊዜ እንደሚቋቋም የህወሓት ቃል አቀባይ ተናገሩ
ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ለትግራይ ህዝብ ሲባል ለውጥ ለመቀበል የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል
የተደራዳሪ ቡድኑ መሪ “የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ድረስ በትግራይ አሉ” ብለዋል
የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከመንግስት እና ህወሓት ሰላም ስምምነት ትግበራ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ጋር ተገናኝተው የተወያዩት ከቀናት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ውይይቱ የስምምነቱን አፈጻጸም የተገመገመበትና ቀጣይ አቅጣጫ የተቀመጠበት እንደበርም ነበር የተገለጸው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጋር የነበረውን ውይይት በተመለከተ ለትግራይ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የህወሓት ተደራዳሪ ቡድንን የሚመሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ “ጊዜያዊ መንግስት”ን በአጭር ጊዜ የማቋቋም ጉዳይ የውይይቱ አንዱ አንኳር ጉዳይ ነበር ብለዋል፡፡
ጊዜያዊ መንግስትን የማቋቋም ጉዳይ የፕሪቶሪያው ስምምነት አካል ከመሆኑ በተጨማሪ ትግራይን እያስተዳዳረ የሚገኘው ፓርቲ ሲያስበው የቆየ ጉዳይ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ለትግራይ ህዝብ ሲባል ለውጥ ለመቀበል የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት አቶ ጌታቸው “በለውጥ አስፈላጊነት ላይ የሚጠራጠር አመራር የለም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
“ጠመንጃ እየተሸከምን ዘላለም መኖር አንችልም” ሲሉም አክለዋል።
የትግራይ ተዳራዳሪ ቡድን መሪው አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በሚሊዮኖች የሚቀጠሩ የትግራይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው በተለመደው መልኩ መቀጠል እንዳመይቻል ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ይህን ይበሉ እንጅ በትግራይ ይዋቀራል ስለተባለው ጊዜያዊ መንግስት ስብጥር እና የሚኖረው ውክልና ያሉት ነገር የለም፡፡
የኤርትራ ወታደሮች መውጣት ጉዳይ ?
የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ መውጣትን ጉዳይ የሰላም ስምምነት ትግበራ አስተባባሪ ኮሚቴው የመከረበት ሌላው አጀንዳ እንደነበርም አንስተዋል አቶ ጌታቸው፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ከአብዛኛው የትግራይ አከባቢ እንዲወጡ ቢደረጉም አሁንም ድረስ በትግራይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
“በወታደራዊ ዩኒት ደረጃ በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀሱባቸው የትግራይ አከባቢዎች እንዳሉ እናውቃለን”ም ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፡
የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበን “በመንግስት በኩል እንዲወጡ ጥያቄ እንደቀረባለቸውና ሲወጡም ምንም አይነት ግርግር ሳይፈጥሩ እንዲወጡ ለማድረግ ዝግጅት አድረገን ነው የሸነናቸው የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል”ም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጋራ የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር ተቆጣጣሪ ቡድን በተንቀሳቀሰባቸው የተወሰኑ አከባቢዎች ማረጋጋጥ የቻለውም ቢያንስ በዋና መስመሮች ላይ የነበረ የኤርትራ ኃይል እንደወጣ መሆኑም አቶ ጌታቸው የሰላም ስምምነቱን አፈጸጸም ያለው ተስፋ ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ የገለጸችው በቅረቡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በቅርቡ የኬንያ ጉብኝታቸው ወቅት በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "የኤርትራ ወታደሮችን በተመለከተ ወደ ድንበር አከባቢ እንደተመለሱ እንዲሁም ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውን እናውቃለን" ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራን ወታደሮች ከትግራይ የማስወጣቱን ጥያቄ ማቅረብ የሚችለው ሌላ ማንም ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ መሆኑ በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር ጴጥሮስ ጸጋይ በቅረቡ መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ከሩሲያው የዜና ወኪል አርአይኤ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደሩ፤ ይህን ያሉት አሜሪካ የኤርትራ ወታደሮችን ከትግራይ እንዲወጡ መጠየቋን በመቃወም ነበር፡፡
ሁለት አመታት በፈጀው ደም አፋሳሹ ሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች ጎን እንደተሰለፉ የሚነገርላቸው የኤርትራ ኃይሎች በከባድ የመብት ጥሰቶች ሲከሰሱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡