ማንቸስተር ሲቲ የቀረቡበት ከ100 በላይ ክሶች ምን ያስከትሉበት ይሆን?
ሲቲ ከ2009 እስከ 2018 ፈጸማቸው የተባሉ የህግ ጥሰቶች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቀርበዋል
የቀረቡት ክሶች ክለቡን ከፕሪሚየር ሊጉ እስከማሳገድ የሚደርስ ውሳኔን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተገምቷል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ክስ በሚቀርበበት ማንቸስተር ሲቲ ላይ ከ100 በላይ የፋይናንስ ህግ ጥሰቶችን አግኝቼበታለሁ ብሏል።
ሊጉ ለአራት አመታት በገለልተኛ ኮሚሽን አጣርቼ ድርሼበታለሁ ያለውን ክስ በዛሬው እለት አቅርቧል።
ክለቡ ምርመራው ከተጀመረበት ታህሳስ 2018 ጀምሮ ትብብር አለማድረጉንም ነው ፕሪሚየር ሊጉ የገለጸው።
ማንቸስተር ሲቲ በቀረበበት ክስ ተጠያቂ እንዲሆን ከተወሰነበት ነጥብ ከመቀነስ እስከ ሊጉ የሚያሰናብት ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል ተነግሯል።
ሲቲ በበኩሉ በሊጉ ክስ መደነቁንና ክሱ ሙሉ በሙሉ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታውቋል።
ፕሪሚየር ሊጉ የጀርመኑ ዴር ስፔግል ጋዜጣ ይዞት የወጣውን ሚስጢራዊ ሰነዶች መነሻ አድርጎ ምርምራውን ሲጀምር ፥ ሲቲ ተራ ውንጀላ ነው በሚል ማስተባበሉ ይታወሳል።
ጋዜጣው ያወጣውን መረጃም “የክለቡ የኢሜል የመልዕክት ልውውጦች በህገወጥ መንገድ በመዝረፍና ከአውድ ውጭ በመተርጎም የተዘጋጀ ነው” በሚል ማጣጣሉም አይዘነጋም።
ሲቲ ዛሬ የቀረበበት አብዛኛው ክስ ከተጫዋቾች ዝውውርና ደመወዝ ጋር በተያያዘ ግልጽ መረጃን ማጋራት አልፈለገም፤ ፍትሃዊ የጨዋታ ደንብንም ደጋግሞ ጥሷል የሚል ነው።
ክለቡ በፈረንጆቹ 2008 በአቡ ዳቢ ዩናይትድ ግሩፕ ባለቤትነት ከተያዘ በኋላ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣ የሊጉን የፉክክር መንፈስ አበላሽቷል በሚል ሲከሰስ ቆይቷል።
በ2020ም የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በገንዘብ አቅሙ የእግር ኳስ ፍትሃዊነትን አደጋ ላይ ጥሏል የሚል ክስ አቅርቦበት እንደነበር የዩሮ ስፖርት ዘገባ ያወሳል።
ማህበሩ ከአውሮፓ መድረክ ለሁለት አመት እንዳይሳተፍ የሚከለክል ውሳኔ ቢያሳልፍበትም፥ ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ የእግር ኳስ ገላጋይ ፍርድ ቤት (ካስ) ወስዶ አሽሮታል።
ዛሬ በፕሪሚየር ሊጉ የቀረበበትን ከ100 በላይ ክስም በእውቅ ጠበቆቹ አማካኝነት እንደሚያስቀለብሰው ነው የሚጠበቀው።
ማንቸስተር ሲቲ በአቡ ዳቢ ዩናይትድ ግሩፕ ከተያዘ በኋላ ስድስት የፕሪሚየር ሊግ፣ ሁለት የኤፍ ኤ፣ ስድስት የካራባኦ እና ሶስት የኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጭዎችን አንስቷል።
ክለቡም በ2021 ለመጀመሪያ ጊዜ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ደርሶ በቼልሲ መሸነፉ አይዘነጋም።
ሮቤርቶ ማንቺኒ፣ ማኑኤል ፔሌግሪኒ እና ፔፕ ጋርዲዮላም እየተፈራረቁ ክለቡን በአሰልጣኝነት መርተውታል።
በነዚህ 15 አመታት ውስጥ ሲቲ ትርፋማነቱ እያደገ ሄዷል፤ በ2021 – 2022 የውድደር ዘመን የክለቡ ጠቅላላ ገቢ 613 ሚሊየን ፓውንድ የደረሰ ሲሆን፥ 42 ሚሊየን ፓውንድ አትርፏል።
ባለፉት ሁለት አመታትም ሪያል ማድሪድን በልጦ የአለማችን ሃብታሙ ክለብ ለመሆን በቅቷል።
ከ2008 ጀምሮ ለተጫዋቾች ዝውውር 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ፓውንድ ያወጣው ማንቸስተር ሲቲ፥ የእንግሊዝን የዝውውር ክብረወሰን ሁለት ጊዜ ሰብሯል።
በ2008 ብራዚላዊውን የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ሮቢንሆን በ32 ነጥብ 5 ሚሊየን ፓውንድ ሲያዛውረው የእንግሊዝ ትልቁ ዝውውር ነበር።
ክለቡ በ2021 ጃክ ግሪሊሽን ከአስቶንቪላ በ100 ሚሊየን ፓውንድ በማዛወርም ክብረወሰኑን ይዟል።
ሲቲ በረብጣ ዶላር ተጫዋቾችን ማዛወሩ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ፉክክርን የአንድ ፈረስ ያደርገዋል ያሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ሲያነሱ ይደመጣል።