ቱርክ የ7 ቀናት የሀዘን ቀን አወጀች
በሀገሪቱ በአሰቃቂው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለማሰብ ነው የሀዘን ቀኑ የታወጀው
3 ሺህ የሚጠጉ ህንጻዎችን ያፈራረሰው ርዕደ መሬት ቱርክ ከ1999 ወዲህ ያስተናገደችው አውዳሚው አደጋ ነው ተብሏል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የሰባት ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን አወጁ።
ፕሬዝዳንቱ በትናንትናው እለት በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ለማሰብ ነው የሀዘን አዋጁን ያወጁት።
የቱርክ ባንዲራ እስከ ቀጣዩ ሳምንት ድረስ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል።
በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት በቱርክ ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ የነፍስ አድን ስራው ባለመጠናቀቁም የሟቾቹ ቁጥር እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል።
በአደጋው ከ2 ሺህ 800 በላይ ህንጻዎች መፈራረሳቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን፥ ይህም ከፈረንጆቹ 1999 ወዲህ የደረሰ አሰቃቂ አደጋ ያደርገዋል ብለዋል።
ኤርዶሃን ከ9 ሺህ በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተው የነፍስ አድን ስራዎችን መከወናችን ስለመቀጠላቸውም ተናግረዋል።
አንካራ ከ45 ሀገራት እንዲሁም ከሰሜት አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና ከአውሮፓ ህብረት የአጋርነት መልዕክት እንደደረሳትም ነው ያነሱት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቱርክ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 6 ሆኖ የተመዘገበ ርዕደ መሬት በዛሬው እለት ማስተናገዷ እየተዘገበ ነው።
አደጋው ያደረሰው ጉዳት ስለመኖሩ ግን አልተጠቀሰም።
ቱርክ ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ክፉኛ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
በፈረንጆቹ 1999 ኢዝሚት በተሰኘች ከተማ የደረሰ ርዕደ መሬት ከ17 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት መንጠቁ የሚታወስ ነው።
በ2011ም በምስራቃዊቷ ቫን ከተማ ከ500 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ርዕደ መሬት መከሰቱን ሮይተርስ ዘግቧል።