የአሜሪካው ዴልታ አየር መንገድ በቅርቡ መጠነኛ አደጋ ለደረሰባቸው መንገደኞች ለእያንዳንዳቸው 30 ሺህ ዶላር እከፍላለሁ አለ
አየር መንገዱ ከአንድ ሳምንት በፊት በቶሮንቶ ኤርፖርት ግጭት አጋጥሞት ነበር

አንድም ሰው ባልሞተበት በዚህ አደጋ 21 መንገደኞች መጠነኛ ጉዳት አስተናግደዋል ተብሏል
የአሜሪካው ዴልታ አየር መንገድ በቅርቡ መጠነኛ አደጋ ለደረሰባቸው መንገደኞች ለእያንዳንዳቸው 30 ሺህ ዶላር እከፍላለሁ አለ።
ዴልታ አየር መንገድ ከአሜሪካ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ሲሆን በያዝነው ሳምንት መግቢያ ላይ በካናዳዋ ቶሮንቶ አደጋ አጋጥሞት ነበር።
አየር መንገዱ አደጋው ያጋጠመው ከአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ወደ ካናዳዋ ቶሮንቶ 80 መንገደኞችን አሳፍሮ ለማረፍ ሲሞክር ነበር።
አውሮፕላኑ ቶሮንቶ ኤርፖርት ካረፈ በኋላ የመንጠር እና የክንፍ ግጭት ባጋጠመው ወቅት 21 መንገደኞች የአካል ጉዳት እንዳጋጠማቸው ተገልጿል።
ከዚህ ውስጥ አንዱ መንገደኛ እስካሁን ህክምና ላይ ነው የተባለ ሲሆን አየር መንገዱ ለሁሉም ተሳፋሪዎች 30 ሺህ ዶላር ካሳ እከፍላለሁ ብሏል።
አየር መንገዱ ለሁሉም ተሳፋሪዎች ካሳ ለመክፈል የወሰነው አካላዊ ጉዳት ከደረሰባቸው መንገደኞች በተጨማሪም ክስተቱ ፍርሀት፣ ድንጋጤ እና ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል በሚል ነው።
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ አየር መንገዱ ላጋጠመው አደጋ መንስኤው ምን እንደሆነ የካናዳ እና አሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጣናት በጋር ምርመራ እያደረጉ ነው።
በሰሜን አሜሪካዎቹ ካናዳ እና አሜሪካ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተደጋጋሚ የአውሮፕላን አደጋ እያጋጠመ ይገኛል።
በአሜሪካ ብቻ ባጋጠሙ አራት አደጋዎች ከ80 በላይ መንገደኞች ህይወታቸውን አጥተዋል።