የአሜሪካ ድብደባን ተከትሎ የመን ራሷን መከላከሏን ትቀጥላለች ሲሉ ሀውቲዎች ተናገሩ
የአሜሪካ ጦር እንደገለጸው በሰንዓ እና በየመን ጠረፋማ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የሀውቲ ይዞታዎች ላይ ድብደባ ፈጽሟል
የሀውቲ ታጣቂዎች እስራኤል የባህር እንቅስቃሴ እንዳይኖራት ለመገደብ በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመሩ ከአመት በላይ ሆኗቸዋል
የአሜሪካ ድብደባን ተከትሎ የመን ራሷን መከላከሏን ትቀጥላች ሲሉ ሀውቲዎች ተናገሩ።
የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች ቃል አቀባይ መሀመድ አዝዱልሰላም አሜሪካ በዋና ከተማዋ ሰንዓ ባሉ ይዞታዎች ላይ ማክሰኞ በርካታ ድብደባ ካደረሰች በኋላ የመን ራሷን መከላከሏን እንደምትቀጥል ተናግሯል።
የአሜሪካ ጦር እንደገለጸው ሰኞና ማክሰኞ እለት በሰንዓ እና በየመን ጠረፋማ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የሀውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ ድብደባ ፈጽሟል።
የአሜሪካ ባህር ኃይል መርከቦች እና አየር ኃይል በሀውቲ ማዘዣ እና መቆጣጠሪያ ጣቢያ እና በዘመናዊ መሳሪያ ማምረቻ እና ማከማቻ ቦታዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ ኤክስ ገጹ ገልጿል።
በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች እስራኤል የባህር እንቅስቃሴ እንዳይኖራት ለመገደብ በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመሩ ከአመት በላይ ሆኗቸዋል። ሀውቲዎች ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት በጋዛ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሀውቲዎች እስካሁን በፈጸሟቸው ጥቃቶች ሁለት መርከቦች የሰጠሙ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
አሜሪካ የተወሰኑ ሀገራትን በማስተባበር በሀውቲዎች ጥቃት እየሰነዘረች ያለችው በመርከቦች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም በማሰብ ነበር።
ሀውቲዎች ባለስቲክ ሚሳይል በማስወንጨፍ በእስራኤል ላይ ጥቃት እያደረሱ ናቸው። እስራኤል ሀውቲዎች እየፈጸሙ ያሉትን ጥቃት የማያቆሙ ከሆነ የሀማስ፣ ሄዝቦሃ እና የሶሪያው በሽር አላሳድ አይነት እጣፋንታ ይገጥማቸዋል ስትል አስጠንቅቃለች።