ጉቴሬዝ የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በዲሞክራቲክ ኮንጎና በቀጠናው ሰላም ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት አደነቁ
በቀጠናው "ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ" በሚደረጉ ጥረቶች፤ ተመድ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል ዋና ጸሃፊው
ዋና ጸሃፊው፤ በዲ.አር ኮንጎ የሚገኙ ሁሉም የታጠቁ ቡድኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፖለቲካው ሂደት እንዲሳተፉም አሳስበዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም፣ መረጋጋትና ልማትን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት አደነቁ፡፡
የዋና ጸሃፊው ተባባሪ ቃል አቀባይ ኤሪ ካኔኮ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከሆነ፤ ዋና ጸሃፊው የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ የቀጠናው መሪዎች ለዲሞክራቲክ ኮንጎ ሰላም ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል፡፡
ጉቴሬዝ በቀጠናው ሃይል እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተሰማራው የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መካከል "ውጤታማ ቅንጅት" እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸውም ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ዋና ጸሃፊው፤ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ ሁሉም የሀገር ውስጥ የታጠቁ ቡድኖች በፖለቲካው ሂደት ውስጥ "ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲሳተፉ" እና ሁሉም የውጭ ታጣቂ ቡድኖች "ትጥቅ ፈትተው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደየመጡበት ሀገር እንዲመለሱ" ሲሉም አሳስበዋል።
ወታደራዊ ያልሆኑ እርምጃዎችን ጨምሮ “የግጭቱን መንስኤዎች” በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዋና ጸሃፊው፤ ውጥረቶችን ለማርገብ በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ቀጣይነት ያለውና ግልጽ ውይይት እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡
በቀጠናው "ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም የሰላም እና የጸጥታ ድሎችን ለማጠናከር" በሚደረጉ ጥረቶች፤ የተባበሩት መንግስታት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ዋና ጸሃፊው ያሉት፡፡
እንደፈረንጆቹ 2017 በሰሜን ምስራቅ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ኮንጎ (ዲ.አር.ሲ) ጁጉ ግዛት የተቀሰቀሰው ግጭት የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ መሆኑና ከ230 ሺ በላይ የሀገሪቱ ዜጎች ማፈናቀሉ የሚታወቅ ነው፡፡