ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሩዋንዳ ጋር ወደለየለት ጦርነት ልትገባ እንደምትችል አስጠነቀቀች
ኮንጎ ኤም 23 የተሰኘው አማጺ ቡድን በሩዋንዳ ይደገፋል የሚል ዕምነት አላት
ሩዋንዳ በበኩሏ የአማጺ ቡድኑ ጉዳይ የኮንጎ የውስጥ ጉዳይ ነው ስትል ክሱን ውድቅ አድርጋለች
ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሩዋንዳ ጋር ወደለየለት ጦርነት ልትገባ እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡
የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ተሸከዲ ከእንግሊዙ ፋይናንሺያል ታየምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ሀገራቸው ከሩዋንዳ ጋር ወደለየለት ጦርነት ልታመራ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየተባባሰ መሄዱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ሩዋንዳ ኤም 23 የተሰኘውን አማጹ ቡድን እየረዳች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ሩዋንዳ ኤም 23 አማጺ ቡድንን መርዳቷን ከቀጠለች ወደ ጦርነት መግባታችን አይቀሬ ነው፣ ይሕ ሲሆን ቁጭ ብለን አናይም ደካሞችም አይደለንም” ብለዋል ፕሬዝዳንት ተሸከዲ፡፡
ሩዋንዳ ኤም 23 አማጺ ቡድንን በጦር መሳሪያ፣በደህንነት መረጃዎች እና ሌሎች ድጋፎች እየረዳች ነው የሚሉት ፕሬዝዳንቱ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢኮኖሚ ፍላጎትም እንዳላት አክለዋል፡፡
የሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መሪዎች ማለትም ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ተሸከዲ ፖል ካጋሜ የፊታችን ረቡዕ በአንጎላ መዲና ሉዋንዳ ተገናኝተው ለመመምከር ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ካጋሜ ኤም 23 የተሰኘውን አማጺ ቡድን እየረዱ መሆናቸውን ሊያምኑ እንደሚገባም ፕሬዝዳንት ተሸከዱ ገልጸዋል፡፡
የዲሞክራቲክ ኮንጎን የማዕድን ማወጫ መሰረተ ልማቶችን እያወደመ ያለው ኤም 23 የተሰኘው አማጺ ቡድን በሩዋንዳ እንደማይደገፍ ከዚህ በፊት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ መናገራቸው አይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንት ካጋሜ በተደጋጋሚ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚቀርብባቸውን ክስ ያስተባበሉ ሲሆን ጉዳዩ የኮንጎ የውስጥ ጉዳይ ነው እኛን አይመለከትም ብለዋል፡፡
ዲሞክራቲክ ኮንጎ ኤም 23 የተሰኘው አማጺ ቡድን ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የሩዋንዳ አየር መንገድ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ እገዳ ጥላለች፡፡