ከስልጣን ለመነሳት 9 ቀን የቀራቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከወዲሁ ከስልጣን እንዲነሱ ጥያቄ ቀረበ
በ25ኛው ማሻሻያ መሰረት ከስልጣን ካልተነሱ ኢምፕችመንት እንደሚካሔድ የኮንግረሱ አፈ ጉባዔ ገልጸዋል
ፕሬዝዳንቱ ተነስተው ምክትላቸው በተጠባባቂነት እንዲመሩ የሚጠይቅ የውሳኔ ሀሳብ ዛሬ ድምጽ ይሰጥበታል
የአሜሪካ ኮንግረስ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ትናንት በሰጡት አስተያየት ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ እና የካቢኔ አባላት ፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከስልጣን እንዲያወርዱ ለሕግ አውጪዎች ሀሳብ ቀርቧል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን ካልቻሉ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ምክትል ፕሬዝዳንቱ በተጠባባቂ ፕሬዝዳንትነት እንዲያገለግል በሚደነግገው በ25ኛው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ መሰረት ፣ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ 9 ቀናት ብቻ የቀሯቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሥልጣን እንዲወርዱ ነው የተጠየቀው፡፡
ደጋፊዎቻቸው ለአመጽ እንዲወጡ እና የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ የሆነውን ካፒቶል ሂልን ሰብረው እንዲገቡ ማድረጋቸው ነው ፕሬዝዳንቱ በድጋሚ ከሥልጣን እንዲነሱ ጥያቄ ያስነሳባቸው፡፡ ማይክ ፔንስ እና ሌሎች የካቢኔ አባላት ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን የማያነሱ ከሆነ ፣ ኮንግረሱ ከዚህ ቀደም ያደረገውን የኢምፒችመንት ተግባር እንደሚፈጽምም ፔሎሲ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ እና የትራምፕ ካቢኔ ፣ አለቃቸውን እንዲያሰናብቱ የሚደነግግ የውሳኔ ሀሳብ ዛሬ ጥር 03 ቀን 2013 ዓ.ም በኮንግረሱ ድምጽ እንደሚሰጥበት እና ለጥያቄው ፔንስ በ24 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጡ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡ ይህ ካልሆነ ፕሬዝዳንቱን በኮንግረስ ክስ ፣ የኢምፒችመንት ሂደትን በመጠቀም የሥልጣን ጊዜያቸው ከማለቁ በፊት እንዲወርዱ የማድረግ ጥረት ይጀመራል ሲሉ የኮንግረሱ አፈ ጉባዔ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ስልጣናቸውን ለግል ጥቅም ተጠቅመዋል እና በኮንግረሱ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ኮንግረሱ በኢምፒችመንት ሂደት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከስልጣን እንዲነሱ ውሳኔ አሳልፎ በሴኔቱ ድጋፍ ሳያገኝ መቅረቱ ይታወሳል፡፡
“ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ ዴሞክራሲ እና ሕገ መንግሥት ላይ ግልጽ ስጋት ደቅነዋል” ያሉት አፈ ጉባዔዋ ፔሎሲ “ቀናት በሄዱ ቁጥር ስጋቶቹ እየተባባሱ በመሔዳቸው ቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስለማይታወቅ ፈጣን እርምጃ መወሰድ አለበት” ብለዋል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በኢምፒችመንት ሂደት ከኃላፊነት ከተነሱ ዳግም ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም፡፡ 9 ቀናት ብቻ ቢቀሯቸውም ከስልጣናቸው በኢምፒችመንት እንዲነሱ ኮንግረሱ የመሯሯጡ ዋነኛ ምክንያትም ለዚሁ ነው፡፡
በትራምፕ ጥሪ መሰረት በደጋፊዎቻቸው በካፒቶል ሂል የተፈጸመውን ድርጊት ተከትሎ ከዴሞክራቶች በተጨማሪ አንዳንድ የሪፓብሊካን ፓርቲ ሴናተሮችም ፕሬዝዳንቱ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ካፒቶል ሂል ላይ በትራምፕ ደጋፊዎች በተፈጸመው አመጽ አንድ የካፒቶል ፖሊስን ጨምሮ የ 5 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡