በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን የሚቃወም ሰልፍ በአዲስ አበባ ተካሄደ
በሰልፉ "እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ፣ ሰላም ይስፈን፣ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም" የሚል መልእክት ተላልፏል
አለም አቀፍ ተቋማት ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን ወንጀል እንዲያጋልጡም ተጠይቋል
በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን የሚቃወም ሰልፍ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተካሄደ።
ሰልፉ "እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ፣ ሰላም ይስፈን፣ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም" በሚል መሪ ቃል በመስቀል አደባባይ ታከሂዷል።
በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጀነት በተካሄደው ሰልፍ ላይም የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በርካታ የስራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ታድመዋል።
በሰልፉ ላይ “የምዕራባውያን ሚዲያና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የተዛባ ዘገባቸውን ያቁሙልን፣ በአፋርና አማራ ክልል በሴቶችና ህጻናት ላይ የደረሱ ጥቃቶች እና ጅምላ ጭፍጨፋ ፍትህ ይሻሉ” የሚሉ መልእክቶች ተላልፈዋል።
በሰልፉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የሴቶችና ህፃናት ጥቃት 'ይብቃ' ብላችህ ለተነሳችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም “ህወሓት በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየበት ጊዜ በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመው ግፍ፣ግዲያና ዘረፋ የከፋ ነው” ብለዋል።
“የህወሓት ቡድን አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ለማመን የሚከብድ ግፍና ሰቆቃ የፈፀመባቸው ሲሆን ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትንም አውድሟል” ሲሉም ተናግረዋል።
አለም አቀፍ ተቋማትና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን ወንጀል እንዲያጋልጡም ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።