በአዲስ አበባ መከላከያን የሚደግፍ እና ህወሓትን የሚቃወም ሰልፍ ተካሄደ
ሀገራዊ ምርጫውንና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚደግፉ ሀሳቦችም በሰልፉ ላይ ተንፀባርቀዋል
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ከተማዋ ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን ገልጸዋል
በአዲስ አበባ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደግፍ እና ህወሓትን የሚቃወም ሰለፍ ተካሄደ።
በአዲስ በአበባ ከተማ የወጣቶች ማህበር እና የሴቶች ማህበር አስተባባሪነት በተካሄደው ሰልፍ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎችም የስራ ኃላፊዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች “መከላከያ ለህዝቦች ደህንነት እና ለህገ መንግስቱ የቆመ ታማኝ ሰራዊት ነው፣ ኢትዮጵያ በጀግኖቿ አፍራ አታውቅም፣ ሉአላዊነታችን ክራታችንና መለያችን፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ መመኘት እንጂ መተግበር አይቻልም” የሚሉ እና ሌሎችም የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት እና የህወሓትን ተግባር የሚቃወሙ መፈክሮችን አሰምተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም “ለህዳሴው ግድብ በአንድነት እንቆማለን፣ ግድባችን ሞልቷል ኢትዮጵያም ከፍ ትላለች፣ የህዳሴ ግድባችን የአይናችን ብሌን ነው” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በተጨማሪም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅ እና ሌሎች በሀገር ደረጃ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚደግፉ ሀሳቦችም በሰልፉ ላይ ተንፀባርቀዋል።
የፌደራል መንግስት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቁ በኋላ በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በመጀመሩ ግጭቱ መከሰቱ ይታወቃል።
ለ8 ወራት የቆየው ግጭት በፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈታ በሚል የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ መንግስት መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወቃል፡፡
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው በትግራይ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል ለሚሉ አካላት ለማሳየትና ተጨማሪ ኪሳራ ሳይደርስ የትግራይ ቀውስ በውይይት እንዲፈታ በማቀዱ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
የመንግስት ጦር መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌንና ሌሎች ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ሮይርስ ዘግቦ ነበር፤ የህወሓት ኃይሎች ለወራት በአማራ ክልል ስር የነበሩት ኮረምና አላማጣን መልሶ ለመቆጣጠር ሙከራዎችን አድርጓል።
ይህን ተከትሎም የአማራ ክልል መንግስት የህወሓት ኃይሎች ወረራ ፈጽመውብኛል በማለት ሌሎች ክልሎች ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ግጭቱ ከአማራና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች አልፎ ወደ አፋር ክልል ተስፋፍቷል፤ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የደቡብና የሲዳማ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ የጸጥታ ሃይላቸውን ወደ ስፍራው አሰማርተዋል።
የፌደራል መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መንግስት ተኩስ አቆሞ እያለ የህወሃት ኃይሎች አሁንም በአማራ ክልል አካባቢ ተኩስ ከፍተዋል፤ መንግስት ተኩስ አቁም ያወጀው ለህዝቡ ሰላም ለመስጠት ሲል እንጅ የግጭት ቦታ ለመቀየር አልነበረም በማለት ምእራባውያን በህወሃት ላይ ያላቸውን አቋም ተችቷል።