ዝነኛዋ ሜጋን መርክል እና ባለቤቷ ልዑል ሀሪ በሎሳንጀለስ ያለውን ቤታቸውን ለተፈናቃዮች ሰጡ
ጥንዶቹ የእሳት አደጋ በደረሰባት ቅንጡ መኖሪያ ቤት አላቸው
የእሳት አደጋው እስካሁን 10 ሰዎችን ሲገድል ከ150 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚወጣ ንብረት አውድሟል፡፡
ዝነኛዋ ሜጋን መርክል እና ባለቤቷ ልዑል ሀሪ በሎሳንጀለስ ያለውን ቤታቸውን ለተፈናቃዮች ሰጡ፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀይል ሀገር በሆነችው አሜሪካ ያጋጠመው የእሳት አደጋ ሰዎችን እያፈናቀለ እና ንብረት እያወደመ ይገኛል፡፡
ይህ እሳት አደጋ ከ100 ሺህ በላይ አሜሪካዊያንን ከመኖሪያ ቤታቸው ያፈናቀለ ሲሆን አሁንም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እሳቱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር በጥረት ላይ ናቸው፡፡
የብሪታንያው ልዑል ሃሪ ሚስት የሆነችው አሜሪካዊቷ የሆሊውድ ተዋናይ ሜጋን መርክል በሎሳንጀለስ የሚገኘው ቤታቸው ተፈናቃዮች እንዲጠለሉበት ፈቅደዋል፡፡
የእሳት አደጋው እስካሁን የጥንዶቹ መኖሪያ ቤት በሚገኝበት ሞንቴሲቶ በተሰኘው መኖሪያ መንደር አካባቢ አለመድረሱን ተከትሎ በአደጋው የተፈናቀሉ ዜጎች በጊዜያዊነት እንዲጠለሉበት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
10 ዜጎችን የገደለው ይህ የእሳት አደጋ እስካሁን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ያልዋለ ሲሆን የሰደድ እሳቱ ፍጥነት ያሳሰባት እና የአሜሪካ ጎረቤት የሆነችው ካናዳ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡
የዓለማችን ኪነ ጥበብ ማዕከል ከሆኑት አንዱ የሆነው የሎስ አንጀለሱ ሆሊውድ ተወናዮችን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች ንብረቶች በእሳቱ በመውደም ላይ ናቸው፡፡
ከነዋሪዎች ባለፈ በበርካታ ፊልሞች ላይ በመተወን አድናቆትን ያተረፉ የዝነኛው የሆሊውድ ተዋናዮች ቅንጡ ቤቶቻቸው በመውደማቸው ምክንያት ሲያለቅሱ ታይተዋል፡፡
ጀኒፈር አኒስተን፣ ቶን ሀንክስ፣ ፓሪስ ሂልተን፣ ቢሊ ክሪስታል፣አዳም ሳንድለር እና ሌሎችም አርቲስቶች ቤታቸው ከተቃጠለባቸው የሆሊውድ ተዋናዮች መካከል ናቸው፡፡
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሎሳንጀለስ ከንቲባ ኬረን ባስ አደጋውን አልተቆጣጠሩም፣ ነዋሪዎች ንብረታቸውን እና ህይወታቸውን እንዳያጡ በቂ የአመራር ድጋፍ አላደረጉም በሚል ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል፡፡