የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ስርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ያስቀመጣቸው ቅጣቶች ምን ይመስላሉ
አዋጁ ከ300-500 ሺህ የገንዘብ እና እስከ 10 አመት የሚደርስ የእስር ቅጣትን አስቀምጧል
መንግስት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ በሂደት ለማስቀረት ተከታታይ የዋጋ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል
የነዳጅ ግብይት ስርዓትን ለመቆጣጠር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዲስ አዋጅ በግብይት ሂደት ውስጥ የሚታዩ ህገ ወጥነቶችን ለመቀነስ ያግዛል ተብሎ ታስቧል፡፡
ሀገሪቱን ከፍተኛ የውጭ መንዛሪ ከሚጠይቁ ከውጭ ከሚገቡ ሸቀጦች መካከል አንዱ የሆነው ነዳጅ የዋጋው መጨመር እና መቀነስ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ጉልህ እንደሆነ ይነገራል፡፡
መንግስት በድጎማ የሚያቀርበውን የነዳጅ ምርት በሂደት ሙሉ ለሙሉ ድጎማውን በማንሳት በሚመጣበት ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ አቅዶ ተከታታይ የዋጋ ማሻሻያዎችን በተለያየ ጊዜ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚታዩ ህገወጥነቶችን ይቀርፋል ያለውን አዲስ አዋጅ በምክርቤት አጽድቋል፡፡
አዋጁ በዘረዘራቸው የህግ መተላለፎች መሰረት በገንዘብ እና በእስራት የሚያስቀጡ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡
በአዋጁ መሠረት ከመሸጫ ዋጋ በላይ በመሸጥ የሚፈጸም የመጀመሪያ ጥፋት ከ350 ሺህ - 500 ሺህ ብር ያስቀጣል።
ድርጊቱ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ ደግሞ የገንዘብ መቀጮው ላይ ከ3 እስከ 5 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚኖር ከአዋጁ ያገኝነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአዋጁ መሠረት የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርዓት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ" ማንኛውም ሰው፤ ከ3 - 5 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ350 ሺህ - 500 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል።
የነዳጅ ምርቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ ከ5-7 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ350 - 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ላይ ተመላክቷል፡፡
በአዋጁ መሠረት የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ማጓጓዝ፣ ከተፈቀደለት ማራገፊያ ስፍራ ውጪ ማራገፍ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ማጓጓዝ፤ ከ5 ዓመት - 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከ400 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር ያስቀጣል።
ከሚመለከተው አካል በጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ የነዳጅ ውጤቶችን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች መሸጥ እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ300 - 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ጥፋት ነው።
የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣንን ወይም የሚመለከተውን አካል የቁጥጥር ሂደት መቃወም እና ማሰናከል ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራት እና ከ200 እስከ 500 ሺህ ብር ያስቀጣል፡፡
በሌላ በኩል የነዳጅ መቅጃ መሳሪያዎች የልኬት ሜትር ማስተካከያ ተደርጎበት በፕሎምፕ የታሰረውን መቁረጥ ወይም ልኬቱን ማዛባትም በተመሳሳይ ከ350 እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ደንግጓል።