በመስቀል አደባባይ ሊደረግ ታስቦ የነበረው የአፍጥር ስነ-ሥርዓት በመስተጓጎሉ ም/ከንቲባዋ ይቅርታ ጠየቁ
ስነ-ሥርዓቱ የተስተጓጎለው ከወቅታዊ የደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ ከአዘጋጆቹ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ነው ተብሏል

የጸጥታ አካላት የተንቀሳቀሱት “በፍፁም ለአፍጥር ክልከላ አይደለም” ብለዋል ም/ከንቲባዋ
በትናንትናው ዕለት ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ እና በዙሪያው ጎዳናዎች ላይ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የአፍጥር ስነ-ሥርዓት ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት የይቅርታ መልዕክት “ውድ የከተማችን ሙስሊም ወገኖቻችን ፣ የኢትዮጵያ አደባባዮች የሁሉም ኢትዮጵያዊን ናቸው!” ያሉ ሲሆን አብሮ አንድ ማዕድ በጋራ የተቋደሰ ፤ አደባባይ "የኔ ፣ ያንተ" ብሎ አይጣላም በማለትም አክለዋል፡፡
የአፍጥር ስነ-ሥርዓቱ እንዳይካሔድ የተደረገበትን ምክንያት ሲገልጹም “ወቅታዊ የደህንነት እና የጸጥታ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የቦታው ስፋት እና ርዝመት ውስን እንዲሆን ባቀረብነው ሀሳብ አዘጋጅ ኮሚቴው ባለማመኑ ብቻ መሆኑ ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን” ብለዋል።
ትናንት ምሽት “የሁላችንም ሰላም እና ደህንነት እንዲጠበቅ አስፈላጊ ጥንቃቄ ለማድረግ የጸጥታ አካላት ጥበቃ ለማድረግ ብቻ ነው የተንቀሳቀሱት” ያሉት ምክትል ከንቲባዋ “በፍፁም የአፍጥር ክልከላ አይደለም” በማለት አስተባብለዋል።
በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የአፍጥር ስነስርዓት መካሄዱንም ወ/ሮ አዳነች ገልጸዋል፡፡
ም/ከንቲባዋ “አንዳንድ ሃላፊነት የማይሰማቸው” ያሏቸው አካላት ይህን ጉዳይ “ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ” በማህበራዊ ሚዲያ ማራገባቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተሰማውን ቅሬታ የገለጸበት መንገድ ጨዋነት የተሞላበት እና ሰላማዊ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም አድንቀዋል።
ትናንት በመስቀል አደባባይ ሊደረግ ታስቦ የነበረው የአፍጥር ስነ-ሥርዓት እንዳይደረግ መከልከሉ ብዙዎችን ማስቆጣቱ እና የማህበራዊ ሚዲያው ዋነኛ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡