ከአዲስ አበባ በ250 ኪ.ሜ ራዲየስ ላይ አደጋ ሊፈጥር የሚችል ኬሚካል ተከማችቷል በሚል የተሰራጨው መረጃ ስህተት መሆኑ ተገለጸ
የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ እና በማለፍ ላይ የሚገኙ ኬሚካሎችን ጉዳት ሳያደርሱ ለማስወገድ ጥረት ተጀምሯል

ኬሚካሎቹ ቢፈነዱ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉት እስከ 250 ሜትር መሆኑን ኤጀንሲው ለአል ዐይን ገልጿል
ከፈነዱ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያሰከትሉ የሚችሉ ተቀጣጣይ ኬሜካሎች በብዙ ድርጅቶች መጋዘን ላይ እንደሚገኙ የሚገልጹ ዘገባዎች ከትናንት ጀምሮ በስፋት በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ዜና የተደናገጡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሀሳባቸውን በተለያዩ መንገድ በመግለጽ ላይ ከመሆናቸው በተጨማሪ ስለ መረጃው እውነትነት በመጠየቅ ላይ ናቸው።
አል ዐይን ዜና ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን ስለመረጃው ጠይቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ፣ ዘገባው የተሰራበት መንገድ ስህተት እንደሆነ ነግረውናል።
እውነታው “በአዲስ አበባ ባሉ የስንዴ መጋዘኖች፣ ዩንቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች እና የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን መጋዘኖች አካባቢ ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ እና ሊፈነዱ የሚችሉ ኬሚካሎች ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በተከዘኑባቸው ቦታዎች ቢፈነዱ መጋዘኖቹ ካሉበት ስፍራ ጀምሮ እስከ 250 ሜትር ባሉ ስፍራዎች ውስጥ አደጋ ሊያደረሱ ይችላሉ የሚል ነው” ብለዋል አቶ ሀጂ።
“እኔን ዋቢ አድርገው የተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች አዲስ አበባን ጨምሮ በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ባሉ ከተሞች ላይ አደጋ ሊፈጠር የሚችል ኬሚካል ተከማችቷል የሚል ዘገባ ሰርተዋል። እኔ ለነዚህ የሚዲያ ተቋማት ይሄንን መናገሬን አላስታውስም። በዚያ መንገድ ተናግሬም ከሆነ ግን በአፍ ወለምታ በስህተት ነው ፣ ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል አቶ ሀጂ።
“እነዚህን ኬሚካሎች ለማስወገድ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጋር ጥናቶችን እያካሄድን ነው” ያሉት አቶ ሀጂ በያዝነው ሚያዝያ ወር ውስጥ ጥናቱ ይጠናቀቃል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በጥናቱ ዘጠኝ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል በሶስት ቡድን ተከፍሎ የግብርና ኬሚካሎችን ፣ የኢንዱስተሪ ኬሚካሎችን እና ሌሎች ለተለያዩ አገልግሎቶች በሚል ወደ አገር ውስጥ የገቡ ኬሚካሎችን የመለየት ስራው በመካሄድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከመንግስት እውቅና ውጪ የገቡ ኬሚካሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ጥናቱ ሲጠናቀቅ የሌሎች አገራትን ልምድ ጠይቀን ኬሚካሎችን በፍጥነት እናስወግዳለንም ብለዋል።