የኢትዮጵያን ውጤታማ ተሞክሮ ያገናዘበ አህጉር ዓቀፍ ትስስር ለመፍጠር መግባባት ላይ ተደርሷል
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዳቮስ
ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በአፍሪካ በማረጋገጥ አህጉር~አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታውቀዋል።
በሶስተኛ ቀን ቆይታ በስዊዘርላንድ ዳቮስ "የአፍሪካ ሰላም ግንባታ" በሚል ርዕስ የአፍሪካ መሪዎችን በአንድ መድረክ ያሰባሰበ የገፅ ለገፅ ውይይት ተካሂዷል።
በዚህ ውይይት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፤ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በአፍሪካ በማረጋገጥ ጠንካራ አህጉር~አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር እየሰራች ያለውን ስራ ና ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት መካከል ሰላማዊ ድባብ እንዲሰፍን እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ መስተጋብር እንዲፈጠር በኢትዮጵያ ያልተቋረጠ ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ የሚገዳደሩ ፈተናዎችን በአስተውሎት ለመሻገር እና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት ፅኑ አቋም እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የታደሙት የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ የአህጉሪቱን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የማጥበቅ አጀንዳ ወቅታዊ ምላሽ የሚሻ መሆኑን አስምረውበታል።
አፍሪካ ከሌሎች ክፍለ~አህጉራት ጋር ሊኖራት የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር በሚጠበቀው ከፍታ አለመጠናከሩ ከፊትለፊት ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ በችግሩ ውስብስብነት ዙሪያ መሪዎቹ ተግባብተዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና በቀጠናው የተረጋጋ ሰላም ለመገንባት የተደረሰበትን ውጤት በመልካም ተሞክሮነት ቀርቧል።
በተመሳሳይ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የኢትዮጵያን ውጤታማ ተሞክሮ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር መቃኘት እንደሚገባ በመጠቆም ትርጉም ያለው አህጉር ዓቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በጋራ ለመፍጠር እንደሚተጉ መሪዎቹ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት
በሌላ በኩል ጠንካራ ዓለማቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን የማዘመን ስራ እያከናወነች መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታውቀዋል።
በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተ.አ.ኤ አዘጋጅነት የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓት ዙሪያ ዓለምአቀፍ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የታደሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፤ ኢትዮጵያ ዓለማቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን ለማዘመን በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑምን በዝርዝር አንስተዋል።
ኢኮኖሚያዊ የማሻሻያ ስራዎች መካከል የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን ለማዘመን በመንግስት የተወሰዱት እርምጃዎች የግሉን ዘርፍ የሚያተጋና የሚያነቃቃ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተለያዩ ክፍለ አህጉራት ጋር ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ደረጀቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማት እና አገልግሎቶች በሂደት እንደሚመቻችም ነው የገለጹት።
በመድረኩ የተሳተፉ የተለያዩ ሃገሮች የፖለቲካ እና የቢዝነስ መሪዎች፤ ኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ እና የትራንስፖርት ዘርፍ ለማዘመን የሄደችበት ርቀትን አድንቀዋል። በቀጣይ ኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ እና በትራንስፖርት ዘርፍ በሚፈጠር ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር በቅርበት እንደሚሰሩ ፍላጎታቸውን ገልፀዋል።
በተያያዘ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የኤሚሬቶች ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሼክ አህመድ ቢን ሰኢድ አል ማክቲም ጋር በሎጂስቲክስ እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።