26 ሰብዓዊ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረሱ መሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ
በትግራይ እየተደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባ የአውሮፓ ህብረት መልዕክተኛ ገልጸዋል
ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ ጋር ተወያዩ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይቱ ወቅት አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የመልሶ ማቋቋምና የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ጉዳይ ለልዩ መልዕክተኛው ገለጻ አድርገዋል፡፡
መንግስት አሁን ላይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍና የወደሙ መሰረት ልማቶችን የመገንባት ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በመሆን 26 የሰብዓዊ ድርጅቶች ሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ስራ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን አጋርነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት አቶ ደመቀ የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ክልል ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መግለጫ ፣ በተለይም የበጀት ድጎማውን ለማቆየት መወሰኑን በተመለከተ የመንግስትን አቋም ገልጸዋል፡፡ የህብረቱ ውሳኔ የሰብዓዊ ድጋፎችን በጊዜ እና በውጤታማነት ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት እንዲሁም ከለውጡ በኋላ የተገኙ የልማት ስኬቶችን ቀጣይነት እንደሚጎዳም ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም ህብረቱ ሁኔታውን እንዲረዳና ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች እንድትወጣ እንደ ስትራቴጂክ አጋርነቱ ገንቢ ሚና እንዲጫወት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡
ከሱዳን ጋር ስላለው የድንበር ውዝግብ በሰጡት ማብራሪያ ፣ ከጥቅምት 30 ጀምሮ የነበረውን ክስተት ያስረዱ ሲሆን ፣ ከጥቅምት30 በፊት የነበረው ሁኔታ ተመልሶ (ሱዳን ከያዘችው ቦታ ለቃ) በተጀመሩ ሂደቶች ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን አቋም አንስተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሽ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ፣ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን ድርድር ለመቋጨት ያላትን ዝግጁነት በተመለከተ ለአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛው ገልጸውላቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሌሎች ሃገራትም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መንፈስ ይህንኑ የኢትዮጵያ መንገድ እንዲከተሉ አሳስበዋል፡፡
የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ በበኩላቸው ፣ ህብረቱ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ላለው ሰብአዊ ሁኔታ እየሰጠ ያለውን ምላሽ ይረዳል ያሉ ሲሆን በክልሉ እየተደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ምርመራ እንዲያጠናክር የጠቆሙት ልዩ መልዕክተኛው መካከል በተለያዩ የትብብር ዘርፎች በኢትዮጵያ እና በህብረቱ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ ገልጸዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፡፡