የ1972ቱ የማስታወሻ ልውውጥ እንዲከበር እና የሱዳን ጦር አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከአፍሪካ አገራት ለተውጣጡ አምባሳደሮች ማብራሪያ ሰጥቷል
26 ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች በትግራይ መሰማራታቸው እና በክልሉ የሚገኙት ሁለት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መውደማቸው ተነግሯል
26 የሚጠጉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ለስራቸው የሚያስፈልጋቸው ምቹ ሁኔታ ተሟልቶላቸው በትግራይ ክልል መሰማራታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
አቶ ደመቀ ከውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ ጋር በመሆን በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ እና ከአፍሪካ አገራት ለተውጣጡ አምባሳደሮች በጽህፈት ቤታቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያው የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ የድርድር ሂደት እና የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብን የተመለከቱ ጉዳዮችም ተነስተዋል፡፡
ለትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ በአግባቡ መከፈል መጀመሩን የገለጹት አቶ ደመቀ በባንኮች በኩል የገንዘብ ተደራሽነት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የገበያ እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
አቶ ደመቀ አያይዘውም በክልሉ ስለሚገኙት ኤርትራውያን ስደተኞች ወቅታዊ ሁኔታ አንስተዋል፡፡
የህጻጽ እና ሽመልባ መጠለያ ጣቢያዎች መዘረፋቸውን እና መውደማቸውን የገለጹም ሲሆን ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ውጭ የተበተኑትን ስደተኞች በመሰብሰብ ደህንነታቸው ወደ ተጠበቀባቸው ስፍራዎች ለማዛወር መንግስት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ሚኒስትሩ መንግስት ያሉበትን አሁናዊ ወሳኝ ጉዳዮች በመቋቋም ፍትሃዊ፣ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ያለውን ጥንካሬ እና አቅም ለተጋባዦቹ ማብራራታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ግድቡን የተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ግንባታው በታሰበው ልክ እየተካሄደ መሆኑን እና ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ከመጪው ክረምት ሊዘለል የሚችልበት ምንም አይነት ሁኔታ እንደሌለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለህግ ማስከበር ዘመቻው ወታደሮቿን ወደ ትግራይ ባሰማራችበት ወቅት የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መግባቱን የገለጹት ደግሞ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ ናቸው፡፡
አምባሳደር ወይንሸት ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የኢትዮጵያ መንግስት አቋም መሆኑን ገልጸዋል።
እስከዚያው ድረስ በግልጽ የተቀመጠው የ1972ቱ የማስታወሻ ልውውጥ እንዲከበር እና የሱዳን ጦር አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።