“በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች በኢትዮጵያ አመራርና በአፍሪካ ድጋፍ ይፈታል”- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የሕዳሴ ግድብ ድርደር በወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር መሪነት እንደሚቀጥል ይጠበቃል
39ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ እየተካሄደ ነው
በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን በኢትዮጵያ አመራርነትና በአፍሪካ ድጋፍ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የአፍሪካ ህብረት የአስፈፃሚ ምክርቤት ስብሰባ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዛሬ በተጀመረው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ቅታዊ ሁኔታ ማብራያ መስጠታቸውን አንስተዋል።
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግሮች በራሷ ለመፍታት እያደረገችው ያለውን እንቅስቃሴ እና ዝግጁነት ዙሪያ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማብራራታውን አስታውቀዋል።
“የእኛን ጉዳይ በራሳችን አመራር በአፍሪካ ሕብረት ድጋፍ እንፈታዋለን የሚል አቋም እንደተያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትቹ አስረድተዋል ብለዋል፡፡
ብዙ ሀገሮች የኢትዮጵያን ስኬት እንደሚመኙ እየገለጹ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና የጉባዔው ተሳፊዎችም ይህንን እየገለጹ እንደሆነም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አክለውም፤ የሕዳሴ ግድብ ድርደር በወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር መሪነት ይቀጥላል ብለን እናስባለን ማለታቸውን ጠቅሰዋል።፡፡
“ድርድሩን እኛ ዝግጁ ሆነን እየጠበቅን ነው፤ አፍሪካዊ አጀንዳ በመሆኑ በአፍሪካ ይፈታ የሚለው የቆየ አቋማችን ነው፤ የቀድሞው ናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸው እኛ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ ይፈታ በሚል ከያዝነው አቋም ጋር የተያያዘ ነውም” ብለዋል፡፡
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው አክውም፤ እስከ ነገ ድረስ በሚዘልቀው ስብሰባ የኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ፣ የክትባት ተደራሽነት እና የምርምር ስራዎች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትን የማጠናከር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አብራርተዋል።