አፍሪካውያን በ2022 የአህጉሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሊሰሩ እንደሚገባ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር አሳሰቡ
ከ100 ሚልዮን በላይ አፍሪካውያን ለምግብ እጥረት እና ረሃብ መጋለጣቸውን ጥናቶች ያመላክታሉ
“የተመጣጠነ ምግብ እና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ” የህብርቱ የ2022 ጉባኤ መሪ ቃል ሆኖ ተመርጧል
በ2022 የአህጉሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሁሉም አፍሪካውያን ሊሰሩ እንደሚገባ የአፍካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት አስገነዘቡ።
ሊቀ መንበሩ ሙሳ ፋኪ መሃማት ይህንን ያሉት በ39ኛው የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ ነው፡፡
የአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ ፈተናዎች ተጋርጠውባት ይገኛሉ ያሉት ሙሳ ፋኪ፣ በአህጉሪቱ ያለው የምግብ እጥረትና በተለያዩ ሀገራት የተጋረጠው ረሃብ ለዚህ ማሳያ መሆኑን እንደ አብነት አንስተዋል፡፡
“የተመጣጠነ ምግብ እና የምግብ ዋስትና” ማረጋገጥ አሁን ላይ በአህጉሪቱ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ያለ ዋና አጀንዳ እንደሆነም ሊቀ መንበሩ አስታውሷል፡፡
“የተመጣጠነ ምግብ እና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ” የአፍሪካ ህብርት ጉባኤ የ2022 መሪ ቃል መሆኑ ይታወቃል፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የአፍሪካ ስትራቴጂ ጥናት ማዕከል ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ከ100 ሚልዮን በላይ አፍሪካውያን ለምግብ እጥረትና ረሃብ ተጋልጠዋል፡፡
ቁጥሩ እንደፈረንጆቹ በ2020 ከነበረው የምግብ እጥረትና ረሃብ መጠን የ60 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ማዕከሉ በጥናቱ አመላክቷል፡፡
ጦርነት፣ የኮቪድ ወረርሺኝ፣ የፖለቲካ ቀውስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች በአህጉሪቱ ለተፈጠረው ከፍተኛ የምግብ እጥረትና ረሃብ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ኮነጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ፣ ማሊ፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና ችግር ካለባቸው የአፍሪካ ሀገራት እንደሆኑም የአፍሪካ ስትራቴጂ ጥናት ማዕከል መረጃ ያሳያል፡፡
ለሁለት ቀናት የሚቆየው 39ኛ አፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ጉባዔ በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።
በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳጽ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመትን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት ነው እየተካሄደ ያለው።
ስብሰባው የአገራት መሪዎች፣ የአፍሪካ ሕብረት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ ተቋማትና በሕብረቱ ስር የሚገኙ ተቋማት የሚያደርጉት በሶስተኛው አጋማሽ ዓመት ለሚያደርጉት ጥምር ውይይት አጀንዳዎች የሚቀርቡበት ነው።