ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት ናት- በጠ/ሚ ዐብይ በበዓለ ሲመት የተገኙ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች
በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ መሪዎች ምን አሉ?
“ወደሄዳችሁት ሁሉ አብረናችሁ እንደምንጓዝ ላረጋግጥ እወዳለሁ” የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በዓለ ሲመት ላይ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የጅቡቲ፣የናይጄሪያ፣ የሴኔጋል ፣የኡጋንዳ መሪዎች፤ የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ተገኝተዋል፡፡
መስሪያ ቤታቸው አዲስ አበባ የሆነው አፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማትም በዚህ ስነስርዓት ላይ ታድመዋል፡፡ በዓለ ሲመቱን የታደሙት መሪዎች ንግግር አሰምተዋል፡፡
ዩዌሪ ሙሴቬኒ
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ላለፉት 60 አመታት በአፍሪካ ፓለቲካ መሳተፋቸውን እና ብዙ ነገር መታዘባቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሀገራቸው የፖለቲካ አመለካከት እና የሀይማኖት ልዩነት እንደነበር ገልጸዋል። በሀገራቸው ኡጋንዳ በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ እንደነበር እና እሱንም በፍላጎት ወይም ጥቅም ላይ ወደ ተመሰረተ ፖለቲካ መቀየራቸውን አንስተዋል፡፡
ዩዌሪ ሙሴቬኒ፤ “በኡጋንዳ እኔ ከዚህ ዘር ነኝ፣ አንተ ከዚህ ዘር ነህ ፤እኔ ይህንን ሃይማኖት ነኝ የሚለው ነገር ክፉኛ ጎድቶናል፤ ኡጋንዳውያን በብሄር ክፍፍል ብዙ ተሰቃይተናል” ብለዋል፡፡ "እኛ ኡጋዳውያን የማንነት (የብሔርና የሐይማኖት) ፖለቲካን ገተን የጥቅም ወይም በፍላጎት ላይ የተመሰረተ (interest) ፖለቲካን በመተካታችን ሀገራችን ዩጋንዳን ማዳን ችለናል፤ለኢትዮጵያውያንም የምንመክረው ይህንኑ ነው" በማለት ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ይሄንን እንዲያስተውል ሃሳብ ያነሱት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ንግግራቸውን የጨረሱት የሚሻለው የዘር ፖለቲካ ነው ወይስ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ? በሚል ጥያቄ ነው፡፡
ሳልቫኪር ማያርዲት
የደቡብ ሲዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ባትኖር ኖሮ ደቡብ ሱዳን አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ እንደማትገኝ ገልጸዋል፡፡አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ በሰላማዊ ንግግር እና በውይይት ሊፈታ እንደሚገባ የገለጹት የደቡብ ሱዳኑ መሪ፤ ለሀገራቸው ደቡብ ሱዳን የነጻነት ጉዞ የቀድሞ መሪዎች ማለትም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ፤ መንግስቱ ኃይለማሪያም እና መለስ ዜናዊ እንዲሁም ቀጥሎ የመጡ መሪዎች እገዛ ተለይቷቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም አዲስ አበባ ወደ ተጓዘችበት ቦታ ሁሉ ጁባ አብራ እንደምንጓዝ ተናግረዋል፡፡
እስማኤል ኦማር ጌሌህ
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ፤ የዓለም መንግስታት ማህበር፤የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት መስራች እንዲሁም አሁን ላይ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገራት የምትጠቀስ መሆኗን የገለጹት ደግሞ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ እስማኤል ኦማር ጊሌህ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ዕድገት እንዲጓጓዙ አብነት ሆና የምትጠቀስ መሆኗንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡
ኡሁሩ ኬንያታ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ሰጥቶ፤ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መምረጡን የገለጹት የኬንያው ፕሬዝዳንት፤ ይህንን እውን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ኬንያ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗ አረጋግጠዋልለ፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት እናት እንደሆነች ያስታወሱት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቀች ሀገር እንደሆነችም አስታውሰዋል፡፡ አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና እጣ ፈነታቸውን ለመወሰን ባደረጉት ተጋድሎ ኢትዮጵያ ሁነኛ አጋር በመሆኗ “የሁላችንም እናት ናት” ሲሉም ፕሬዝዳንት ኬንያታ ተናግረዋል፡፡ “እናት ሰላም ካልሆነች ቤተሰብ ሰላም አይሆንም፤ ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፤ ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ማየት እንሻለን” በማለትም ተናረዋል፡፡