አዲሱ የደራርቱ ቱሉ የስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ምን የተለየ ነገር ይዟልʔ
በአትሌት ደራቱ ተሉ የተሰየመው የስፖርት ማሰልጠኛ እና የምርምር ኢንስቲትዩት ተመርቋል
በ1.5 ቢሊየነ ብር የተገነባው ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 800 ሰልጣኞችን መቀበል ይችላል
በአትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው የስፖርት ማሰልጠኛና ምርምር ኢንስቲትዩት በዛሬው እለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
በሸገር ከተማ አስተዳደር ሱሉልታ ክ/ከተማ የተገነባው ማዕከሉ በዛሬው እለት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረ/ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎችም አመራሮች በተገኙበት ተመርቋል።
በምረቃው ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የማዕከሉ ግንታ በ2007 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰው፤ የነበረውን የተወሳሰበ ችግር መንግስት እስኪያስተካክል ድረስ መጓተቱን አስታውቀዋል።
የስፖርት ማሰልጠኛ እና የምርምር ኢንስቲትዩቱ በጀግናዋ አትሌት በተለይም በኦሎምፒክ የአፍሪካ እና የኢትዮጰያ የትልቅ ድል ባለቤት በሆነችው ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ መሰየሙን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በደራርቱ ተሉ የተሰየመው ለመጪው ትውልድ ታሪክን ለማሳየት እና እንደ ደራርቱ ቱሉ ያሉ ጀግኖች ለማፍራት ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በዚህ ስፍራ የሚሰለጥኑ አትሌቶች የደራርቱን ዱካ እንዲከተሉም አሳስበዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ ማዕከሉ በስሟ በመሰየሙ አመስግና፤ ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ የአትሌቲክስ ችግሮች የሚቀርፍ ይሆናል ብለለች።
ኢንስቲትዩቱ በውስጡ ምን ይዟልʔ
በ1 ነጠብ 5 ቢሊን ብር ወጪ የተገነባው፤ የደራርቱ ቱሉ የስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከ40 በላይ ህንጻዎችን በውስጡ ይዟል።
የደራርቱ ቱሉ የስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት በ14 የስፖርት አይነቶች በአንድ ጊዜ 800 ሰልጣኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ ይችላል።
ኢንስቲትዩቱ፤ 24 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ትምህርት ቤት፣ 198 የስፖርቶኞች ማደሪያ ክፍሎች፣ እንዲሁም የጥናትና ምርምር ክፍሎች አሉት።
በተጨማሪም 5200 ተመልካች መያዝ የሚችል እና 250 ሰው የሚያስተናግድ ዘመናዊ አዳራሾች፣ 2 የውሃ መዋኛ ገንዳ፣ 6 ሜዳ ቴኒስ መጫወቻ፣ 6 የመረብ ኳስ ሜዳ፣ 4 የቅርጫት ኳስ ሜዳ፣ 2 የእጅ ኳስ ሜዳ፣ የአትሌቲክስ የመሮጫ እና የእርምጃ ውድድር መለማመጃ ትራክ እንዲሁም 3 የእግርኳስ ኳስ መጫወቻ ሜዳዎችን በውስጡ ይዟል።
እንዲሁም ዘመናዊ ጂምናዚየም እና የጤና ማእከልም በውስጡ ይዟል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የስፖርት ማሰልጠኛ ማእከል ማሟላት የሚገባውን ሁሉ አማልቷል ያሉት የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃፊ አቶ ማቲዮስ ሰቦቃ፣ በኢትዮጵያ ደረጃ ግዙፉ ነው ብለዋል።