አትሌቷ ለኢትዮጵያ በተለያዩ የሩጫ ውድድሮች ከ15 በላይ ሜዳሊያዎችን አበርክታለች
ጃፓን አትሌት ደራርቱ ቱሉን የወርቅ ኒሻን ሸለመች፡፡
በአዲስ አበባ የጃፓን ኢምባሲ እንደገለጸው የጃፓን መንግስት ለአትሌት ደራርቱ ቱሉ የወርቅ ኒሻን መሸለሙን ገልጿል፡፡
ጃፓን አትሌት ደራርቱ ቱሉን የሸለመችው በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል በስፖርታዊ ዲፕሎማሲ እና ልውውጥ ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሖኑት አትሌት ደራርቱ ቱሉ የወርቅ ኒሻን ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከስፖርት ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከሁለት ዓመት በፊት ህይወታቸው ካለፈው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን በማሰባሰብ የውይይት መድረክ አመቻችተው ነበር፡፡
በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. በ2019 የጃፓን ስፖርት ኤጀንሲ ኮሚሽነር የሆኑትን ሚስተር ሱዙኪ ዳይቺን እና የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ እና ፓራሊምፒክ ጨዋታዎችን በኃላፊነት ይመሩ ከነበሩት ወይዘሮ ሃሺሞቶ ሴይኮ ጋር ተገናኝተው ስለ ቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ተወያይተው እንደነበር ተገልጿል።
በአትሌቲክስ ስፖርት የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ተደርጎ በነበረው ስምምነት በ2019 የካሳማ አትሌቲክስ አካዳሚ አሰልጣኝ በመሆን በጃፓን የቶኪዮ ማራቶን ሶስት ተከታታይ ድሎች በማሸነፍ ከሚታወቁት አትሌት አበበ መኮንን ወደ ካሳማ ከተማ በመላክ በአሰልጣኝነት ያላቸውን ልምድ እንዲያካፍሉም አትሌት ደራርቱ ጥረት እንዳደረጉም ተገልጿል፡፡
ጃፓን ይህን እውቅናና ሽልማት ከፈረንጆቹ 1875 ጀምሮ ለውጭ ሃገር ዜጎች በጃፓን መንግስት የሚሰጥ የሽልማት ስነ ስርዓት ሲሆን የአሁኑ ሽልማት ለኢትዮጵያዊያን ሲሰጥ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
“የኢትዮጵያ ህዝብ አንፈልግሽም ልቀቂ ካለኝ ስልጣኔን በደስታ እለቃለሁ”-ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ
አትሌት ደራርቱ ቱሉ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በስፖርቱ ዓለም በማስጠራት ጀምራ ለኅብረተሰብ ፍቅርና አንድነት መጎልበት ተግታለች በሚል ነሀሴ 2014 ላይ ከባህርዳርዩንቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማግኘቷ ይታወሳል፡፡
ከ50 ዓመት በፊት በአርሲ በቆጂ የተወለደችው ደራርቱ ቱሉ ለአፍሪካ ሴት አትሌቶች ፈር ቀዳጅ አትሌት ስትሆን በዓለም አቀፍ የስፖርቱ ማህበረሰብ የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ንግስት በመባልም ትጠራለች፡፡
አትሌት ደራርቱ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በፈረንጆቹ 1990 ላይ ቡልጋሪያ በተካሄደ የወጣቶች ውድድር ላይ ማግኘቷ አይዘነጋም።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በተካሄዱ ውድድሮች ለሀገሯ ከ15 በላይ የወርቅ ብር እና ነሀስ ሜዳሊያዎችን በተለያዩ ውድድሮች ላይ ለሀገሯ አስገኝታለች።