አብንን ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ እንደታሰሩ ቤተሰባቸው ተናገሩ
ደሳለኝ ጫኔ የባህር ዳር ህዝብን ወክለው ምክር ቤቱን መቀላቀላቸው ይታወሳል
የምክር ቤት አባሉ ትናንት ምሽት ከመኖሪያ ቤታቸው በፌደራል ፖሊስ መታሰራቸው ተገልጿል
አብንን ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ እንደታሰሩ ቤተሰባቸው ተናገሩ።
በ2013 በተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በባህርዳር ከተማ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን ወክለው ተወዳድረው የተመረጡት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) መታሰራቸውን ቤተሰባቸው ተናግሯል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ቤተሰብ አባል ለአልዐይን እንዳሉት ከሆነ "ትናንት ጥር 22 ቀን 2016 ዓ .ም ምሽት 3:30 ላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት የጸጥታ ሀይሎች መጥተው ደሳለኝ ጫኔን ለጥያቄ እንፈልግሀለን ብለው ወስደውታል" ብለውናል።
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ታስረው እንደሚገኙ የነገሩን እኝህ የቤተሰብ አባል የፌደራል ፖሊሶቹ ለጥያቄ እንፈልግሀለን ከማለት ውጪ ምንም ያሉት ነገር የለም ሲሉም ነግረውናል።
ዛሬ ጠዋት ጀምሮም ተጨማሪ የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ መኖሪያ ቤቱ መጥተው ፍተሻ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ሰምተናል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ጀይላን አብዲ ስለ ጉዳዩ መረጃ እንዲሰጡን ላቀረብንላቸው ጥያቄ "አሁን ላይ ስለ ጉዳዩ መረጃ የለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡
በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ አዋጅ ምክንያት በማድረግ ሌላኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ከስድስት ወራት በፊት መታሰራቸው ይታወሳል።
ለስድስት ወራት ይቆያል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጠናቀቂያ ጊዜው የደረሰ ሲሆን ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም አዋጁ ስድስት ወራት ይሞለዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለማብቃቱም ሆነ መራዘሙን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ የለም