አብን በአማራ ክልል ተኩስ አቁም ታውጆ የሰላም ንግግርና ድርድር እንዲጀመር ጥሪ አቀረበ
በትጥቅ ትግል የተሰለፉ ሁሉ ለሰላማዊ ንግግርና ድርድር አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ አብን ጠይቋል
አብን ተፋላሚ ሃይሎች ማህበራዊ ቀውሶች እንዳይባባሩ መተላለፊያ መንገዶች ክፍት እንዲያደርጉ አሳስቧል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ተኩስ አቁም ታውጆ የሰላም ንግግርና ድርድር እንዲጀመር ጥሪ አቀረበ።
አብን ትናንት ባወጣው መግለጫው “የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች በመንግስት በኩል ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ አለማግኘታቸው አለፍ ሲልም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቹን ማንሳቱ እንደ ድክመት መቆጠሩ ህዝቡን ለጦርነትና ለሰላም ዕጦት ተጋላጭ አድርጎታል” ብሏል።
የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም የአማራ ክልል የሚገኝበት ፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ የፖለቲካ ልዩነቶች ከሃቀኛ ውይይትና ድርድር በላይ አይደሉም ብሎ እንደሚያምንም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።
- በአማራ ክልል በተፈጸመ የድሮን ጥቃት መምህራንን ጨምሮ ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን ተመድ ገለጸ
- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ዙሪያ ያወጣው ሪፖርት ከእውነታ ያፈነገጠ ነው- መንግስት
ስለሆነም “ልይነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ የሰለጠነና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ አካሄድ ነው” ያለው አብን፤ መንግስት ከታጠቁ ሀይሎች ጋር ለሰላም ንግግርና ለድርድር በር እንዲከፍትና ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል።
በሂደቱም የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሙህራንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተሳተፉበት፤ ተአማኒ፣ ግልፅ እና አካታች እንዲሁምን ጠይቋል።
“መንግስት የክልሉ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን መድረክ በመፍጠር ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥ የተየቀው አብን፤ “ለሀቀኛ የሰላም ንግግርና ድርድር በሩን ለታጠቁ ሃይሎች እንዲከፍትና አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲታዎጅ ጥሪ እናስተላልፋለን” ብሏል።
በየአካባቢው በትጥቅ ትግል የተሰለፉ አካላት ህዝቡ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ለሰላማዊ ንግግር እና ድርድር አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
ለሁሉም ተፋላሚ ሃይሎች አሁን ያለው የኑሮ ውድነት፣ የገበያ አለመረጋጋትና ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች ተባብሰው እንዳይቀጥሉ፤ መተላለፊያ የሚሆኑ መንገዶች ክፍት እንዲሆኑ እንዲያደርጉም አብን በመግለጫው አሳስቧል።
መንግስት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲዳረስ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያለገደብ ድጋፋቸውን ተደራሽ እንዲያደርጉ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የሀይማኖት ተቋማት በግጭቱ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸውም ጥሪ አቅርቧል።
በግጭቱ ወቅት ለተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ተጣርቶ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፤የተፈናቀሉ ወገኖች እንዲመለሱ ሊደረግ ይገባልም ብሏል።
ሚዲያዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች፤ በግጭቱ ምክንያት ህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኪሳራ ታሳቢ ያደረገና የህዝባችን ፍላጎት የሆነው ሰላም እንዲሰፍን አወንታዊ ሚና እንዲጫወቱም ጠይቋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የምትገኙ የአማራ ተወላጆችና ኢትዮጵያዊያን ሰላማዊ ንግግሮችንና ድርድሮችን እንድታበረታቱ፣ የህዝቡን እሴት መሰረት ያደረገ በሃላፊነት ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርብ እርምጃ እንዲወስዱም ጠይቋል።