ንቅናቄው በተደጋጋሚ ያቀረብኳቸው ጥሪዎች ባለመሰማታቸው አማራ ክልል ወደ ለየለት ቀውስ ገብቷል አለ
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል በፌዴራል የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጫ አውጥቷል።
ግጭቱ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሚጠበቅ እንደነበር የጠቆመው ንቅናቄው፤ ይህ እንዳይሆን በተደጋጋሚ ጥሪ ባቀርብም ጆሮ ዳባ ተብያለሁ ብሏል።
መፍትሄ ይፈልጉ የነበሩ ጥያቄዎች አዳማጭ በማጣታቸው ቅራኔና ምስቅልቅል እንዲፈጠር ሆኗል ሲልም አክሏል።
ለክልሉ ቀውስ "የአማራ ልሂቃን እና የፖለቲካ ኃይሎች እንዲሁም የተለያዩ የሲቪክ አደረጃጀቶች የራሳቸው ድክመት እንዳለ ሁሉ የክልሉ መንግስት እነዚህ አካላት በጋራ እንዳይመክሩና መፍትሄ እንዳያፈላልጉ በስልት መድረክ መነፈጋቸው ተደማሪ ችግር ሆኖ መቆየቱንም አብን ያምናል" ብሏል።
ውጥንቅጡ ሰፊ ምክር የሚሹ አንገብጋቢ የህዝብ ጉዳዮች "ድንገት የተላለፉ ውሳኔዎች" ያስከተሉት ውጤት ነውም ሲል አስታውቋል።
ፓርቲው ለሀገር አንድነትና ለህዝብ ህልውና ታግለዋል ያላቸው የፋኖ አባላቶች፤ በችኩል መፈረጃቸውና ሚናቸውን መነጠቃቸው "መከፋትን" ፈጥሯል ሲል መንግስትን ለክፍተቱ ወቅሷል።
በአማራ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ በዋናነት የፌዴራሉና በተለይም የክልሉ መንግስት ያልሰሯቸው ስራዎች ድምር ውጤት ነው ሲል ገልጿል።
መሆኑ ኃላፊነትን በመውሰድ ችግሮቹን በዘለቄታዊነት በውይይት ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥ አብን ጠይቋል።
አብን በአማራ ክልል "ተደራራቢ ተግዳሮቶች" ተዳምረው ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ስር እንዲወድቅ ሆኗል ብሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲመራ የጠየቀው ንቅናቄው፤ በአጭር ግዜ እንዲነሳም ጠይቋል።
አዋጁን ለማስፈጸም የተሰማሩ አካላትም ከማንነት ተኮር ፍረጃዎች፣ ወከባዎች፣ ዘፈቀደ እስራትና አካላዊ ጥቃቶችን እንዲታቀቡ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
ጦርነት ዘላቂ ጥቅምን ለማረጋገጥ አስቻይ ባለመሆኑ ለሰላማዊ የፖለቲካ መፍትሄዎች ተገቢው ስፍራ እንዲሰጠውም አደራ ብሏል።
በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው የፌደራል መንግስት የክልሉን የሰላም ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ነበረበት እመልሳለሁ ሲል መግለጹ ይታወሳል።