አብን አላማው "ትጥቅ ማስፈታት" ነው ያለውን የመንግስት ውሳኔ በጽኑ ተቃወመ
አብን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔው እንዲሰርዙ ጠይቋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን የማፈረስ ውሳኔ "ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን" እንደሚተገበር ገልጸዋል
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ትናንት ባወጣው መግለጫ የልዩ ሀይል አደረጃጀቶችን ለማፍረስ በመንግስት የተላለፈው ውሳኔ በሁሉም ክልሎች በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ እንደማይሆን መገምገሙን ገልጿል።
አብን "የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት እና መበተን" ነው ብሏል።
- የተደረሰው ውሳኔ "ለሕብረ ብሄራዊ አንድነት" ሲባል እንደሚተገበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
- ልዩ ኃይል እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትናው እለት ባወጡት መግለጫ የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን የማፈረስ ውሳኔ "ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን" እንደሚተገበር እና በሁሉም ክልሎች እንደሚፈጸም ገልጸው ነበር።
አብን ውሳኔው በሁሉም ክልሎች ተፈጻሚ ይሆናል የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ "እውነትነት የሌለው" ነው ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።
አብን ቀደም ሲል የአማራ ክልሉ ልዩ ሀይልን ለማፍረስ የተላለፈው ውሳኔ ክልሉን እንዲሁም ሀገሪቱን ወደ አለመረጋጋት ሊያስገባት እንደሚችል ስጋቱንም ገልጾ ነበር።
በአማራ ክልል ተገማች ጥቃት ያሉባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የገለጸው አብን የክልሉን ልዩ ሀይል በጥድፊና እና መተማመን ሳይፈጠር ማፍረስ ወቅታዊ ውሳኔ አይደለም ማለቱ ይታወሳል።
አብን መንግስት ውሳኔውን ለመተግበር በመንቀሳቀሱ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን እና እንቅስቃሴ መገታቱን ጠቅሷል።
አብን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔው እንዲሰርዙ ጠይቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ ክልል ፖሊስ ሰራዊት እንዲካተቱ ውሳኔ ሲደረግ ተገቢ ዝግጅት ተደርጎበት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩ የትጥቅ መፍታት ሳይሆን የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ተገቢ ስልጠናና ትጥቅ ወደሚያገኙበት እና ሀገርን በተሻለ ሁኔታ ወደሚያገለግሉበት መዋቅሮች ማስገባት እንደሆነ ገልጸዋል።
መንግስት ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ውሳኔውን የሚቃወሙ ሰልፎች በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች እየተካሄዱ ነው።