ወጣቶች በላሞች ለመረገጥ የሚሯሯጡባት የህንድ መንደር
ከዳዋሊ (የብርሃል በዓል) አስቀድሞ የሚካሄደው በከብቶች የመረገጥ ስነስርአት የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ጀምሯል
በፈቃዳቸው ከብት በላያቸው ላይ የሚነዳባቸው ሰዎች የፈቀዱት ሁሉ እንደሚሆንላቸው ያምናሉ
ህንዳውያን ከሳምንት በፊት የብርሃን በዓል ነው የሚሉትን የዳዋሊ በዓል በተለያዩ ስነስርአቶች አክብረዋል።
በማድያ ፕራዴሽ ግዛት ቢዳቫድ በተባለች መንደር ያለው አከባበር ግን ለየት ያለ ነው ይላል ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው።
በመንደሯ ወጣቶች መሬት ላይ ተኝተው ላሞች በላያቸው ላይ ረግጠዋቸው እንዲያልፉ የሚደረግበት የቆየ ልማድ አለ።
በፈቃዳቸው በላሞች የሚረገጡት ሰዎች መጻኢያቸው የተቃና የልባቸው የሚሞላ ይሆን ዘንድ ነው በላሞች የሚረገጡት።
በአካባቢው በላሞች የሚያመልኩ በርካታ ሰዎች እንዳሉ የተነገረ ሲሆን፥ ከ330 ሚሊየን በላይ አማልዕክት በላሞች ውስጥ ስለሚኖሩ በነእርሱ መረገጥ የአማልዕክቱን በረከት ያስገኛል ብለው ያምናሉ።
በላሞች ለመረገጥ ፍላጎታቸውን የሚገልጹ ሰዎች ለአምስት ቀናት በጾም እንደሚቆዩ ተገልጿል።
ይሄው በላሞች የመረገጥ ስነስርአት ሲካሄድም የመንደሯ ሰዎች ተሰብስበው በዝማሬና በምስጋና ያጅቧቸዋል ተብሏል።
ህንዳውያን ከጨለማ ወደ ብርሃን እንደሚሸጋገሩበት የሚገልጹት የዳዋሊ (የብርሃን በዓል) ከመከበሩ ከቀናት በፊት የሚከበረው በላሞች የመረገጥ በዓል በየአመቱ የታዳሚው ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው።
በላሞች የሚረገጡት ሰዎች እስካሁን ምንም ጉዳት አላስተናገዱም መባሉም አግራሞትን ያጭራል።