ከ40 አመት በፊት ከተለዩዋት ባለቤታቸው ለመፋታት ለ27 አመታት ፍርድ ቤት የተመላለሱት ህንዳዊ
የፍቺ ጥያቄውን የተመለከተው የህንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለፍቺ የሚያበቃ ምክንያት አላገኘውም ብሎ ውድቅ አድርጎታል
በህንድ ከ100 ትዳር በፍቺ የሚጠናቀቀው አንዱ ብቻ ነው ተብሏል
በህንድ ፍቺ እንደ ጋብቻ ቀላል አይደለም።
በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ፍቺ እንደ ነውር ነው የሚታየው።
የቤተሰብ እና ማህበረሰቡ ግፊት በርካቶች ደስተኛ ባልሆነ ትዳር ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋል።
ባል ወይም ሚስት ፍቺ ቢፈልጉ እንኳን አሳማኝ የበደል ወይም ጥፋት ማስረጃ ማቅረብ ስለሚኖርባቸው በፍርድ ቤት ጥያቄያቸው እምብዛም ተቀባይነት አይኖረውም።
ይህን የሚያስረግጥ ዜና ከሰሞኑ ተሰምቶ መነጋገሪያ ሆኗል።
የ89 አመቱ ከ40 አመታት በፊት ከተለያያት ሚስቱ በይፋ በፍርድ ቤት ለመፋታት ለ27 አመታት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱ ተነግሯል።
ኒርማል ሲንግ ፓኔሳር የተባሉት የቀድሞው የአየር ሃይል አባል አሁን 82 አመት ከሆናቸው ፓራምጂት ካውር ፓኔሳር ጋር በፈረንጆቹ 1963 ነው የተጋቡት።
በጋብቻቸውም ሶስት ልጆችን ቢያፈሩም ከ21 አመታት በኋላ ትዳራቸው ንፋስ ይገባዋል።
የፀቡ ምክንያትም በስራ ምክንያት መራራቃቸውና ባል ሚስቱ እና ልጆቹ ወደኔ ቀረብ ብለው መኖር ይጀምሩ በሚል ያቀረቡት ጥያቄ ነበር።
በመምህርነት ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩት ሚስት ስራዬን ለቅቄ አልመጣም ማለታቸው ልዩነቱን አስፍቶት ተለያዩ።
ፍቺው በፍርድ ቤት የፀና እንዲሆንም ኒርማል በፈረንጆቹ 1996 ወደ ወረዳ ፍርድ ቤት አቤት ይላሉ።
ይሁን እንጂ ባለቤታቸው ፓራምጂት ትዳራቸውን ለማፅናት የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን በመጥቀስ በመከራከራቸው ፍርድ ቤቱ የፍቺ ጥያቄውን ውድቅ አደረገው።
ኒርማል ከህንድ አየር ሀይል በጡረታ ከወጡ በኋላም ከ40 አመት በፊት ከተለዩዋት ሚስታቸው ጋር በፍቺ እንዲለያዩ ላለፉት 27 አመታት ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል።
የ89 አመት አዛውንት የህንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍቺ ጥያቄያቸውን እንዲመለከት ያቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝም የ27 አመት ድካማቸው እንደሚያበቃ ተስፋ አድርገው ነበር።
በ82 አመታቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት ፓራምጂት ፍቺውን እንደሚቃወሙና የ89 አመት ባላቸውን (ቢለያዩም ፍቺው ስላልፀደቀ) ለመንከባከብ ዝግጁ መሆናቸውንና በዚህ እድሜያቸው ፍቺ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
ዳኞችም ትዳር የተቀደሰ ተቋም መሆኑን በመጥቀስና ለፍቺ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት አላገኘንም በሚል የፍቺ ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል።
በህንድ ከ100 ትዳር በፍቺ የሚጠናቀቀው አንዱ ብቻ ነው ተብሏል።