አዛዉንቷ ህንዳዊት በኮሮና ህይወታቸው አልፏል በሚል ነበር ወደ አስከሬን ማቃጠያ ስፍራ የተላኩት
በህንድ እስካሁን ከ270 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። በህንድ ሰው ሲሞት አስከሬንን የማቃጠል የቆየ ባህል አለ።
በህንዷ ማሃራሽትራ ግዛት ነዋሪ የሆኑት የ76 ዓመቷ ሻኩንታላ ጃክዋድ በያዝነው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ ነበር ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት።
እንደ ሜትሮ ዘገባ ከሆነ አዛውንቷ መተንፈስ በመቸገራቸው ሲልቨር ጁብሊ ወደተሰኘው ሆስፒታል ቢላኩም አልጋ በመጥፋቱ ምክንያት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።
ይሁንን የአዛውንቷ ህመም እየጠና በመሄዱ መተንፈስ ማቆማቸውን ሜትሮ ቤተሰቦቻቸውን ጠይቆ የሰራው ዘገባ ያስረዳል።
በዚህም ምክንያት አዛውንቷ ህይወቷ አልፏል በሚል ወደ አስከሬን ማቃጠያ ስፍራ ተወስደው ቤተሰቦቻቸው ቦታው እስኪለቀቅ በመጠባበቅ ላይ እያሉ በድንገት ህይወታቸው አልፏል የተባሉት አዛውንት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።
በዚህ የተደናገጡት የአዛውንቷ ቤተሰቦች መልሰው ወደ ሆስፒታል ይዘዋት መሄዳቸው እና አሁን ላይ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጽል።
ህንድ በሁለተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በመጠቃት ላይ ስትሆን በቀን ከ4 ሺህ በላይ ህንዳዊያን በዚህ ገዳይ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን በማጣት ላይ ናቸው።
ከፍተኛ የኦክስጅን እጥረት ያጋጠማት ህንድ ከተለያዩ ሀገራት እርዳታዎችን በማሰባሰብ ላይ ስትሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን እንዲወስዱ በማበረታታት ላይ ይገኛሉ።
በህንድ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር ከ25 ሚሊዮን በላይ የሆነ ሲሆን በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር ደግሞ ከ275 ሺህ አልፏል።