የዲኤችኤል የጭነት አውሮፕላን ከመኖሪያ ቤት ጋር ተላትሞ በእሳት ተያያዘ
ከጀርመን ላይፕዚሽ የተነሳው አውሮፕላን በሊዩቲኒያ መዲና ለማረፍ ሲቃረብ ነው አደጋው ያጋጠመው
አውሮፕላኑ ከገጨው መኖሪያ ቤት ውስጥ 12 ሰዎችን ያለጉዳት ማስወጣት መቻሉ ተገልጿል
የጀርመኑ የሎጂስቲክ ኩባንያ "ዲኤችኤል" የጭነት አውሮፕላን በሊዩቲኒያ ተከሰከሰ።
በስዊፍት አየርመንገድ የሚተዳደረው የኩባንያው አውሮፕላን በቪልኒየስ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ጥቂት መቶ ሜትሮች ሲቀሩት ነው አደጋው ያጋጠመው።
አውሮፕላኑ መሬት ላይ ሲንሸራተት ቆይቶ ከመኖሪያ ቤት ጋር በመጋጨትም በእሳት መያያዙን የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
አውሮፕላኑ ከግጭቱ በኋላ በእሳት የተያያዘ ሲሆን አንድ የበረራ ቡድኑ አባል ህይወቱ ማለፉን የሊዩቲኒያ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሲኤንኤን ዘግቧል።
አብራሪውን ጨምሮ ሶስት የበረራ ቡድኑ አባላትም ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።
ከጀርመኗ ላይፕዚሽ የተነሳው የጭነት አውሮፕላን የተከሰከሰበት መንስኤ እየተጣራ መሆኑንም የሊዩቲኒያ የብሄራዊ አደጋ አስተዳደር ሃላፊው ቪልማንታስ ቪልካውካስ ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ከመከስከሱ አስቀድሞ ፍንዳታ እንደገጠመው የሚያመላክቱ ጉዳዮች እስካሁን ሪፖርት አለመደረጋቸውንም ነው ለሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና አገልግሎት ኤልአርቲ የገለጹት።
በአውሮፕላኑ ከተገጨው መኖሪያ ቤት ውስጥ 12 ሰዎችን ለማስወጣት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ርብርብ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
የቪሊኒየስ አውሮፕላን ማረፊያ የእሳት አደጋ ሰራተኞች በእሳት የተያያዘው አውሮፕላን ሙሉ በሙሉ እንዳይወድም ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።
አደጋው በቪሊኒየስ ኤርፖርት የበርካታ አውሮፕላኖች የመነሻ ስአት እንዲጓተት ማድረጉ ቢገለጽም የአውሮፕላን ማረፊያው ቃል አቀባይ ግን ሁሉም በረራዎች በተያዘላቸው ስአት ቀጥለዋል ብለዋል።