10 ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ካላቸው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች መካከል ስድስቱ በአሜሪካ ይገኛሉ
የአውሮፕላን ማምረቻ ኢንዱስትሪ የአለም ኢኮኖሚ ወሳኝ አካል ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲሁም እድገትን በማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይነገርለታል፡፡
ይህ ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትን በማፋጠን ለመጓጓዣነት ይውላል፣ የሀገር መከላከያ እና ደህንነትን ይደግፋል ፣ ለአለም አቀፍ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገትም ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው፡፡
በ2034፤ 601.51 ቢሊየን ዶላር ዋጋ እንደሚኖረው የሚጠበቀው አለም አቀፉ የአውሮፕላን ምርት በአሁኑ ወቅት 400 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ነው፡፡
ዘርፉ ለአለም አቀፍ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ አብርክቶ ያለው ሲሆን በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን ገቢ በማድረግ ለአለም አቀፉ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት 4.1በመቶ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ለአመታት በአውሮፕላን ቴክኖሎጂዎች ፣ የመጫን አቅም እና ሌሎችንም ማሻሻያዎች በማድረግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የዘርፉ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትን የኤርባስ እና ቦይንግን የገበያ ድርሻ ለመቀራመት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ብርቱ ፉክክር እያደረጉ ነው፡፡
የተለያዩ ኩባንያዎችን ደረጃ የሚያወጣው ካምፓኒስ ማርኬት ካፕ ድረ ገጽ በዚህ ወር ባወጣው ሪፖርት የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች በሚያገኙት ገቢ ፣ በገበያ ድርሻቸው ፣ በትርፍ ህዳጋቸው እና የሰራተኞቻቸውን ብዛት መስፈርት ውስጥ በማስገባት ደረጃቸውን አውጥቷል፡፡
በዚህም ግዙፍ አውሮፕላኖችን በማምረት የሚታወቀው የኔዘርላንዱ ኤርባስ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ 136.53 ቢሊየን ዶላር የገበያ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚው ሆኗል፡፡
ሀኒዌል 130.93 ፣ ቦይንግ 121.1 ቢሊየን ዶላር ድርሻ በመያዝ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከ1 እስከ 10 በተቀመጠው የአውሮፕላን አምራቾች የገበያ ድርሻ ደረጃ አሜሪካ 6 ኩባንያዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ ናት።