ሞተሩ የተበላሸበት አውሮፕላን ጉዳት ሳይደርስበት ማረፉ ተገለጸ
አየርመንገዱ ኢንጂነሮቹ የመጀመሪያ ምርመራ ማካሄዳቸውን እና የሞተር ብልሽት መኖሩን ማረጋገጣቸውን ገልጿል
ባለሁለት ሞተር የሆኑት የእነዚህ አይነት አውሮፕላኖች በአደጋ ጊዜ በአንድ ሞተር እንዲበሩ ተደርገው የተሰሩ ናቸው ተብሏል
ሞተሩ የተበላሸበት አውሮፕላን ጉዳት ሳይደርስበት ማረፉ ተገለጸ።
አርብ እለት ወደ ብርስባኔ ሲበር የነበረው የኳንታስ አየር አየመንገድ አውሮፕላን ከተነሳ በኋላ የሞተር ብልሽት ቢያጋጥመውም የተወሰነ ጊዜ አየር ላይ ዞሮ በሰላም ወደ ሲድኒ ኤየርፖርት ማረፉን ሮይተርስ የሀገሪቱን መገናኛ ብዙኻን ጠቅሶ ዘግቧል።
በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍሮ የነበረው የኤቢሲ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ከፍተኛ ድምጽ ከተሰማ በኋላ ፈጣን መንቀጥቀጥ ተፈጥሮ ነበር ብሏል።
"በአንደኛው የአውሮፕላኑ ሞተር ላይ የሆነ ነገር እንደተከሰተ ግልጽ ነበር። ከእዚያ በኋላ አውሮፕላኑ ወደ ከፍታ ለመውጣት ተቸግሮ ነበር" ሲል የኤቢሲው ጋዜጠኛ ማርክ ዊላሲ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። ኳንታስ አየርመንገድ በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው የነበሩት መንገደኞች እና ሰራተኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ይፋ አላደሰገም።
አየርመንገዱ ኢንጂነሮቹ የመጀመሪያ ምርመራ ማካሄዳቸውን እና የሞተር ብልሽት መኖሩን ማረጋገጣቸውን ገልጿል። የፈነዳው ሞተር ሞተሩን ለመከላከያ ከተሰራው የውጨኛው መሸፈኛ አለመውጣቱንም ኢንጂነሮቹ አረጋግጠዋል።
የፈነዳው ሞተር፣ ሞተሩን ለመከላከል ከተሰራው መያዛ ወይም መሸፈኛ ውጭ ወጥቶ ቢሆን ኖሮ የሞተሩ ፍንጥርጣራዎች በዋናው የአውሮፕላኑ ክፍል ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችሉ ነበር ተብሏል።
የፍላይት ራዳር 24 መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የበረራ ቁጥሩ ኪውኤፍ520 የሆነው የኳንታስ አውሮፕላን ለትንሽ ደቂቃዎች ከዞረ በኋላ ተመልሶ ወደ ሲዲኒ ኤየርፖርት ማረፉን ያሳያል። የአውሮፕላኑ መነሳት እና በእሳት አደጋ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ከዋለው በአውሮፕላን ማኮብኮቢያ ቦታ ላይ ከተፈጠረው የእሳት አደጋ ጋር ተገጣጥሟል።
"ሁለቱ ክስተቶች ስለመገጣጠማቸው ግንኙነት ስለመኖሩ አሁን ላይ ግልጽ አይደለም፤ ምርመራዎች ቀጥለው እየተካሄዱ ናቸው" ብሏል ኤየርፖርቱ።
የአውስትራሊያ ሰንደቅ አላማ ተሸካሚ የሆነው የኳንታስ አየርመንገድ አውሮፕላን አስፈላጊ ሂደቶች ከተከናወኑ በኋላ በሰላም ማረፉን የገለጸው ኤየርፖርቱ ሞተሩ በምን ምክንያት እንደተበላሸ እንደሚመረምር ገልጿል።
እንደ ፍላይት ራዳር መረጃ ከሆነ አውሮፕላኑ 19 አመት የሆነው ቦይንግ 737-800 ሞዴል ነው። የአውሮፕላኑ ሞተር የተሰራው የጂኤ ኤሮስፔስ እና የፈረንሳዩ ሳፍራን የጋራ ድርጅት በሆነው በሲኤፍኤም ኢንተርናሽናል ነው።
ባለሁለት ሞተር የሆኑት የእነዚህ አይነት አውሮፕላኖች በአደጋ ጊዜ በአንድ ሞተር እንዲበሩ ተደርገው የተሰሩ ናቸው ተብሏል።