የአሜሪካ ሚሳኤሎች አልዘዋሪሂን ያለ አንዳች የጎላ የፍንዳታ ድምፅ የገደሉት
መነጋገሪያ ከሆኑ ሰሞነኛ ቀዳሚ የሚዲያ ጉዳዮች መካከል አንዱና ቀዳሚው የአልቃይዳው መሪ አል ዛዋሂሪ መገደል ነው።
የቀድሞው የሽብር ቡድኑ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን የቅርብ ሰውና አማካሪ አልዛዋሂሪ በቢላደን እግር ተተክቶ ቡድኑን መምራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ሆኖም ላለፉት 20 ገደማ ዓመታት ልክ እን ቢላደን ሁሉ አልዛዋሪን ስታድን የነበረችው አሜሪካ መግደሏን ትናንት ሰኞ አስታውቃለች።
አልዛዋሂሪ በአፍጋኒስታን መገደሉን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይፋ አድርገዋል።
ሆኖም የ71 ዓመቱ ግብጻዊ ቀዶ ጠጋኝ ሐኪም አገዳደል አሁንም ብዙዎችን እንዳስደመመ ነው። አልዛዋሂሪ ያለ አንዳች ከባድ ፍንዳታ እና የከፋ ጉዳት እንደተገደለ መነገሩም ብዙዎችን ለግርምት ዳርጓል።
ከሞቱ አሟሟቱ እንዲሉም በሁኔታው የተገረሙ ብዙዎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑን ጨምሮ ስለሁኔታው እየጠየቁ ነው።
ቁንጮው የሽብር ቡድን መሪ እንዴትና በምን ተገደለ የሚሉ መጣጥፎችን በማስነበብም ላይ ይገኛሉ።
ሰው አልባዎቹን (ድሮን) ጨምሮ ሌሎችም የጦር አውሮፕላኖች ዒላማቸውን የሚያደባዩት እንደ ነጎድጓድ በሚያስገመግም ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ታጅበው ነው የሚለው ዘ ናሽናል አልዛዋሪን የተገደለበት ሚሳኤል ግን ድምፅ አልባ እና ዒላማውን ብቻ ነጥሎ የመታ ነው የሚል ሰፊ ሃተታን ይዞ ወጥቷል።
አልዛዋሪ በመኖሪያ ቤቱ በረንዳ ላይ ሳለ የተገደለበት ሚሳኤል ምንነቱ በውል ባይገለጽም አዲስና የተለየ ነው ሲል የሚያትተው ዘ ናሽናል የጦር ተንታኞች መሳሪያው ምናልባትም 'በራሪው ጊንሱ' ወይም
'R9X Hellfire' በሚል ከሚታወቁ እጅግ ዘመናዊ የአሜሪካ የሚሳኤል ጦር መሳሪያዎች መካከል አንዱ ሳይሆን እንዳልቀረ መናገራቸውን አስቀምጧል።
መሳሪያው 'ኒንጃ ሄልፋየር' የሚል ቅጽል መጠሪያ እንዳለውሞ ነው ሃተታው የሚጠቁመው።
የጦር መሳሪያው ምንነት
'በራሪው ጊንሱ' በሚል ይጠራሎል የተባለለት እጅግ ዘመናዊው የሚሳኤል ጦር መሳሪያ ግለሰቦችንና የተለዩ ዓላማዎችን ነጥሎ ለመምታት በማሰብ የተሰራ ነው።
ዒላማውን ነጥሎ ለመምታት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ይነገራል። በመኪና ውስጥ ከሚጓዙ ሰዎች እንኳን አንዱን ብቻ ነጥሎ ለመምታት ያስችላልም ነው የሚባለው።
ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ሌሎች የሚሳኤል ዝርያዎች ቢኖሩም ይኼንኛው ግን የተለየ ስለመሆኑ ይነገርለታል።
መሳሪያው ወደ መሬት ተምዘግዝጎ ዒላማውን የሚመታና 45 ኪሎ ግራም የሚመዝን አረርን እንደሚሸከምም ነው አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ለዎል ስትሪት ጆርናል የተናገሩት።
ሆኖም አሜሪካ ስለ በራሪው ስለሚባለው ጦር መሳሪያ አንዳችንም ነገር አላለችም። ስለ አሰራሩና ስለ ስሪቱ የተባለ ነገርም የለም።
አልዛዋሪን በመግደሉ ውጥን ንጹሃንን ከጉዳት ለመታደግ የሚያስችል ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን ግን አልሸሸገችም።
ባሳለፍነው ነሐሴ በፈጸመችው ተመሳሳይ ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ 10 ገደማ ንጹሐን መገደላቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ትችትንና ውግዘትን ማስተናገዷ ይታወሳል።
በመሆኑም ይህን ተከትሎ አልዛዋሪን ለመግደል ለግለሰባዊ ዒላማዎች በሚል በፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን እንደተሰራ የተነገረለትን 'በራሪው ጊንሱ'ን መጠቀሟ ተነግሯል።
የቀድሞው የአል ቃይዳ መሪ ቢን ላደን በፕሬዝዳንት ኦባማ ትዕዛዝ በፈረንጆቹ 2011 በፓኪስታን አቦታባድ መገደሉ ይታወሳል።