ታሊባን አሜሪካ በካቡል የፈፀመችውን የድሮን ጥቃት አወገዘ
አሜሪካ በካቡል በወሰደችው እርምጃ የአልቃይዳ መሪ አይማን አል ዘዋሂሪን መግደሏን አስታውቃለች
ታሊባን የአልቃይዳው መሪ መገደሉን ባይገልጽም ጥቃቱ በመኖሪ ቤቶች ላይ የተፈፀመ ነው ብሏል
ታሊብን በአሜሪካ በአፍጋኒስታኗ ዋና ከተማ ካቡል የፈጸመችውን የድሮን ጥቃት አወገዘ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፤ የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤ በካቡል በወሰደው እርምጃ የአልቃይዳ መሪ አይማን አል ዘዋሂሪ መገደሉን አስታውቀዋል።
አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ የሚገኘው ታሊባን የአሜሪካን ጥቃት ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፤ ጥቃቱ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ የተፈፀመ ነው ብሏል።
የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሉላህ ሙጃሂድ በሰጡት መግለጫ፤ አሜሪካ በካቡል የሚገኝ ሸርፑር የመኖሪያ መንደር ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ የአሜሪካን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፤ የአልቃይዳው መሪ አይማን አል ዘዋሂሪ መገደሉን ግን ከመናገር ተቆጥበዋል ነው የተባለው።
አፍጋኒስታንን እየመራ የሚገኘው የታሊብን መንግስት የደህንነት ተቋም በጥቃቱ ላይ ምርመራ በማድረግ የመጀመሪያ ሪፖርት ይፋ ማድረጉን እና በምርመራውም ጥቃቱ በአሜሪካ ድሮን የተፈፀመ መሆኑን እንደተረጋገጠ ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
የጥቃቱ ኢላማ ምንም ይሁን ምን የአፍጋኒስታን መንግስት እንደሚያወግዘው ያስታወቁት ቃል አቀባዩ፤ መሰል እርምጃዎች የአሜሪካን እና የአፍጋኒስታንን ግንኙነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ናቸው ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሽብር ቡድኑ መሪ፤ የአሜሪካ የስለላ ተቋም (ሲአይ ኤ) በፈጸመው የድሮን ተልዕኮ መገደሉን አረጋግጠዋል።
የቀድሞውን መሪ ኦሳማ ቢላደንን በመተካት አል ቃይዳን ሲመራ የነበረው ትውልደ ግብፃዊው አይመን ዘዋሂሪን የተገደለው በአፍጋኒስታን ካቡል መሆኑንም ጆ ባይደን ተናግረዋል።
አይማን አል ዘዋሂሪን የተገደለው የሽብር ቡድኑን ቁልፍ መሪዎችን ኢላማ በማድረግ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት እንደሆነም ተገልጿል።
የአል ዘዋሂሪን መገደልን ተከትሎ በቀጣይ የሽብር ቡድኑን ማን ይችላል በሚል የተለያዩ መላምቶች በመነሳት ላይ ናቸው። አሁን ላይ እየወጡ ባሉ መረጃዎች ሌላኛው ግብጻዊ ሰይፍ አል ማስሪ ሊተካ እንደሚችል ግምቶች በመውጣት ላይ ናቸው።