የአልቃኢዳው መሪ አይመን አልዘዋሂሪ እንዴት ሊገደል ቻለ?
አልዘዋሂሪ የተገደለው ቤቱ በር ላይ ተቀምጦ ባለበት ከሰው አልባ አውሮፕላን በተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎችን ነው
አልዘዋሂሪ የኦሳማ ቢን-ላደን ህልፈትን ተከትሎም አል-ቃይዳን ሲመራ የቆየ ሽብር ቡድን መሪ እንደነበር ይታወቃል
አሜሪካ የአልቃኢዳውን መሪ አይመን አልዘዋሂሪን በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ባካሄደችው የድሮን ጥቃት መግደሏን አስታውቃለች፡፡
የአልዘዋሂሪ መገደል ለአልቃኢዳ፤ ከኦሳማ ቢን ላደን መገደል በኋላ ያጋጠመው ከፍተኛ ወታደራዊ ኪሳራ እንደሆነም ነው በመገለጽ ላይ ያለው፡፡ ለመሆኑ ለበርካታ ዓመታት በአሜሪካ የስለላ መረብ ሲፈለግ የቆየው “አይማን አልዘዋሂሪ እንዴት ሊገደል ቻለ…?” የሚለው አሁንም የበርከካች ጥያቄ ነው፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት አንድ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን እንደሚሉት ከሆነ የአልቃኢዳውን መሪ አይመን አልዘዋሂሪን የመግደል ዘመቻን "ትጋትና እና ታታሪነት የታየበት ድንቅ ስራ ነው" ሲሉ በአጭሩ ይገልጹታል፡፡
ላለፈው አንድ አመት አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ከወጣች በኋላ ባለስልጣናት በሀገሪቱ ውስጥ የአልቃይዳ ምልክቶችን ሲከታተሉ ቆይተዋል በማለት የኦፕሬሽኑ ዝረዝር መግለጫ የሰጡት ከፍተኛ ባለስልጣኑ ፤ አልዘዋሂሪ አፍጋኒስታን ውስጥ ስለመኖሩ የአሜሪካ የጸረ-ሽብር እና የስለላ ቡድኑ አባላቱ ካረጋገጡ በኋላ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት በአሜሪካ መንግስት ከውሳኔ መደረሱ ተናግረዋል፡፡
ከውሳኔው በኋላ አልዘዋሂሪ በአፍጋኒስታን የትኛው ቦታ እንደሚገኝ ለማወቅ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት የአልዘዋሂሪ ቤተሰብ - ሚስቱ፣ ሴት ልጁ እና ልጆቹ - በካቡል በሚገኘው "ደህንነቱ የተጠበቀ ቤት" ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ መቻሉንና ብዙም ሳይቆይ አልዘዋሂሪ በተመሳሳይ ቤት እንደሚገኝ የአሜሪካ የስለላ ባለስልጣናት ማረጋገጣቸውም አክለዋል ባለስልጣኑ፡፡
ከፍተኛ ባለስልጣኑ አልዘዋሂሪ የሚገኝበት ቤት ከታወቀ በኋላ በሃምሌ 1 ቀን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ጄክ ሱሊቫንና የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊልያም በርንስን ጨምሮ የአሜሪካ የስለላ ጠበብቶች በዋይት ሀውስ (White House Situation Room) ውስጥ ስለታቀደው ኦፕሬሽን ፤ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ገለጻ ማድረጋቸውንና የተሻለውን እርምጃ ለመገምገም ስብሰባ መቀመጣቸውም አስታውሷል፡፡
በዋይት ሀውስ በተደረገው ስብሰባ ጀ-ባይደን፤ እርምጃው ከመወሰዱ በፊት ኦፕሬሽኑን ለመምራት የየአልዘዋሂሪ የአኗኗር ዘይቤን ለማወቅ የሚያስችሉ ዝርዝር መረጃዎች ጠይቀው ፤ በስለላ ቡድኑ ዝርዝር መረጃ እንደቀረበላቸውም ነው የተገለጸው፡፡
“ የአሜሪካ የደህንነትና የስለላ ባለሙያዎች፤ አልዘዋሂሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች በ“ደህንነቱ የተጠበቀ ቤት” በረንዳ ላይ የመታየት ልምድ አንዳለው ከበርካታ ምንጮቻቸው መረዳት፣ ማየትና ማረጋገጥ ቻሉ”ም ይላሉ ከፍተኛ ባለስልጣኑ፡፡
አልዘዋሂሪን እቤቱ በረንዳ ላይ ሳለ የመግደል ዘመቻን በልበ ሙሉነት ማከናወን እንደሚችሉ ያረጋገጡት፤ የአሜሪካ የደህንነትና የስለላ ቡድን አባላቱ የአልዘዋሂሪ ቤተሰብ ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ በሚል የአልቃይዳው መሪ የሚገኝበት ደህንነቱ የተጠበቀ ቤት ግንባታ ዘዴን እና ባህሪን ምርመራ ማካሄዳቸውም ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ የስለላ ቡድን አባላት ደህንነቱ የተጠበቀ ቤት ግንባታ ዘዴን እና ባህሪን የተመለከተ አሰፈላጊውን ምርመራ ካካሄዱ በኋላ በ71 አመቱ የአልቃኢዳ መሪ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የመጨረሻውን የይለፍ ፍቃድ መሰጠቱም ነው የገለጹት ።
ከፍተኛ ባለስልጣኑ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት “ሃምሌ 30 ቀን 2022፤ አልዘዋሂሪ እቤቱ በር ላይ ተቀምጦ ባለበት ከአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን በተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎችን ሊገደል ችለዋል” ብለዋል፡፡
አልዘዋሃሪ ከቀድሞው የአልቃኢዳ መሪ ቢንላደን ጋር በመሆን የ 9/11 ጥቃትን የመራ ሲሆን አሜሪካ ለረጅም አመታት ስታፈላልገው የቆየች የሽብር ቡድኑ መሪ ነው።
የኦሳማ ቢንላደን ህልፈትን ተከትሎም አል-ቃይዳን ሲመራ ቆይቷል።
አልዘዋሂሪ እንደፈረንጆቹ በጥቅምት 2000 በኤደን የአሜሪካ የባህርኃይል አውዳሚ ላይ በተሰነዘረ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 17 የአሜሪካ መርከበኞችን የገደለውን ጥቃት እንደመራም ይነገርለታል፡፡
በተጨማሪም፤ ለ223 ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆኑት በ1998 በኬንያ እና ታንዛኒያ በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በማስተባበር አል- ዘዋሂሪ ሃላፊነት እንዳለበት ይነሳል።