የዲያጎ ማራዶና ሀኪሞች በነፍስ ማጥፋት የቀረበባቸው ክስ የፍርድ ሂደት ተጀመረ
7 ሀኪሞች ለእግር ኳስ ተጫዋቹ በቸልተኝነት ተገቢውን ህክምና ባለመስጠት ክስ ቀርቦባቸዋል

ተከሳሾቹ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ እስከ 25 አመት የሚደርስ እስር ይጠብቃቸዋል
የነርቭ ቀዶ ሐኪም እና የአዕምሮ ህክምና ባለሙያን ጨምሮ ሰባት የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ለዲያጎ ማራዶና በቂ የህክምና አገልግሎት አልሰጡም በሚል ክስ ለፍርድ ቀርበዋል።
የ1986 የአለም ዋንጫ አሸናፊ ከእግር ኳስ ታላላቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በህዳር 2020 ከቦነስ አይረስ ወጣ ብሎ በሚገኝው መኖሪያ ቤት ውስጥ በ60 አመቱ በልብ ህመም ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡
የህክምና ባለሙያዎቹ ለማራዶና አስፈላጊውን የህክምና እገዛ ባለማድረግ ህይወቱ በቸልተኝነት እንዲያልፍ በማድረግ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ጉዳዩን እየተከታተሉት የሚገኙት ከሳሽ አቃቤ ህግ ፓትሪስዮ ፌራሪ ማራዶና ከመሞቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ትግሪ በተባለችው ከተማ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ማራዶና በዕምሮው ውስጥ የደም መርጋት እንዳጋጠመ እና ቀዶ ጥገና እንዲደረግለትም በሀኪሞች ተወስኖ ነበር፡፡
በተጨማሪም ህክምናውን ሲከታተሉ የነበሩት ሀኪሞች በቤቱ ሆኖ እንዲታከም እና ቀዶ ጥገናም በዛው መኖሪ ቤት ውስጥ እንዲያደርግ የወሰኑት ውሳኔ ለእግር ኳስ ኮከቡ ህልፈት ምክንያት መሆኑን በመጥቀስ ክስ መመስረቱን ነው የገለጹት፡፡
አቃቤህጉ ማራዶና በመኖሪያ ቤት ውስጥ ተገቢውን ህክምና ባለማግኝት በአልጋ ላይ ሆዶ አብጦ ተኝቶ የሚያሳይ ምስል ለፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡
በፍርድ ሂደቱ ላይ ዳልማ እና ጂያኒና የተባሉት የማራዶና ሁለት ሴት ልጆች በፍርድ ቤት ተገኝተው ጉዳዩን ሲከታተሉ ታይተዋል፡፡
ለአራት ወራት ይቆያል በተባለው የፍርድ ሂደት የተከሰሱት 7 የህክምና ባለሙያዎች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 25 አመት እስር ድረስ ሊፈረድባቸው ይችላል፡፡
እግር ኳስ በዘመኑ ካያቸው የምንጊዜም ድንቅ ኮከቦች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ዲያጎ ማራዶና በ1986 የአለም ዋንጫ ያነሳው ብሔራዊ ቡድን አባል ከመሆኑ ባለፈ በ2010 የደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫ የአርጄንቲና ብሔራዊ ቡድንን በአሰልጣኝነት መርቷል፡፡