ባለሙያዎቹ በማራዶና ህክምና ቸልተኝነት አሳይተዋል በሚል ነው የሚከሰሱት
የግል ሐኪሞቹን ጨምሮ ስምንት የህክምና ባለሙያዎች በቀድሞው የአርጀንቲና እግርኳስ ኮኮብ ዲዬጎ አርማንዶ ማራዶና ሞት ሊከሰሱ ነው።
ባለሙያዎቹ በማራዶና የህክምና ሂደት ቸልተኝነት አሳይተዋል በሚል ነው የሚከሰሱት።
በእግር ኳሱ ዓለም ህያው ስምን የተከለው ማራዶና ከሁለት ዓመታት በፊት (በፈረንጆቹ ወርሃ ህዳር 2020) በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል።
ያጋጠመውን የጭንቅላት ደም መርጋት ህመም ተከትሎ በተደረገለት ቀዶ ጥገና አገግሞ ወደ ቤቱ ተመልሶ የነበረው ማራዶና በልብ ህመም ነው የሞተው።
ይህን ተከትሎም ከማራዶና አምስት ልጆች ሁለቱ የአባታቸው አሟሟት ጉዳይ ግድፈት እንዳለው በመጠቆም እንዲመረመርላቸው የሃገራቸውን መንግስት ጠይቀዋል፡፡
የአርጀንቲና ዐቃብያነ ህግጋትም በአሟሟቱ የህክምና ጉድለቶች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል 20 አባላት ያሉት የህክምና ባለሙያዎች ቡድንን አቋቁመው ምርመራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የአንጋፋውን ተጫዋች አሟሟት ጉዳይ የመረመረው የባለሙያዎቹ ቡድንም ባለፈው ዓመት በአሟሟቱ የህክምና ባለሙያዎቹ እጅ እንዳለበት ማረጋገጡ ይታወሳል።
ባለሙያዎቹ ከቸልተኛነት በተጨማሪ ሊሰጡ የሚገባቸውን መድኃኒቶች በወቅቱ አለመስጠታቸውን አረጋግጠናልም ነው የባለሙያዎች ቡድን አባላቱ ያሉት፤ ማራዶና ተገቢው ክትትል ቢደረግለት ምናልባትም በህይወት የመትረፍ እድል እንደነበረው በመጠቆም።
ጉዳዩን ከነ ምርመራ ውጤቱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም በባለሙያዎቹ ላይ የግድያ ወንጀል ክስ እንዲመሰረት አዟል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ሊታይ የሚችልበት ቀን አልተገለጸም እንደ ቪኦኤ ዘገባ፡፡
የባለሙያዎቹ ጥፋተኝነት በፍርድ ቤቱ የሚረጋገጥ ከሆነ እያንዳንዳቸው የ25 ዓመታት እስራት ይጠብቃቸዋል።
ሆኖም የግል ሐኪሞቹን ጨምሮ ስምንቱ ባለሙያዎች ማራዶና በእነሱ ቸልተኝነት ሞቷል መባሉን አስተባብለዋል። የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውንም ነው የገለፁት።
ማራዶና ከአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ጋር የ1986ቱን የዓለም ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።