ማራዶና በ1986ቱ የአለም ዋንጫ የተሸለማት የወርቅ ኳስ ለጨረታ ልትቀርብ ነው
አርጀንቲናዊው ኮከብ እንግሊዝ ላይ በእጁ ባስቆጠራት ጎል (“የእግዜር እጅ”) ይታወሳል
የቀድሞው የናፖሊና ቦካ ጁኒየርስ ተጫዋች ዲያጎ ማራዶና በ2020 ነው ህይወቱ ያለፈው
ዲያጎ ማራዶና በ1986ቱ የአለም ዋንጫ የተሸለማት የወርቅ ኳስ ለጨረታ ልትቀርብ ነው።
በ2020 ህይወቱ ያለፈው አርጀንቲናዊ በሜክሲኮው የአለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በእንግሊዝ ላይ በእጁ ባስቆጠራት ጎል አሁንም ድረስ ይወሳል።
ይህቺ “የእግዜር እጅ” የሚል ስያሜ የተሰጣት ጎል ማራዶና የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች የሚሸለመውን የወርቅ ኳስ እንዲያገኝ ድርሻ ነበራት።
የወርቅ ኳሷ ለረጅም ጊዜ ጠፍታ እንደነበር የሚያወሳው አጉተስ የተባለ አጫራች ኩባንያ፥ አንድ ግለሰብ በፈረንሳይ በ2016 በተካሄደ ጨረታ ከሌሎች እቃዎች ጋር እንደገዛት ይገልጻል።
ግለሰቡ የማራዶና የሜክሲኮ የኮከብ ተጫዋች ሽልማት መሆኗን አልተገነዘበም ነበር የሚሉት የተቋሙ የስፖርት ባለሙያ ፍራንኮይዝ ቴሪ፥ በሂደት በኢንተርኔት አምራቹን በማግኘት የማራዶና ሽልማት መሆኗን ተረድቷል ብለዋል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ማራዶናን እና የአለም እግርኳስ ማህበርን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ከግለሰቡ ጋር በመነጋገር ታሪካዊ የወርቅ ኳሷን በሰኔ ወር መጀመሪያ በፈረንሳይ ለጨረታ ለማቅረብ መወሰኑ ተገልጿል።
በ”ሚሊየኖች” ትሸጣለች የተባለችው የማራዶና የሜክሲኮ ሽልማት የጨረታ መነሻ ዋጋዋ ግን አልተጠቀሰም።
ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በ1986ቱ የአለም ዋንጫ አምስት ጎሎችን አስቆጥሯል።
በሩብ ፍጻሜው ከእንግሊዝ ጋር ሲጫወቱ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠሩ የሚታወስ ሲሆን፥ የመጀመሪያዋ በእጁ ያስቆጠራት ጎል በአርጀንቲናውያን ዘንድ “የእግዜር እጅ” ይስቆጠራት ተብላለች።
አምስት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን አልፎ ያስቆጠራት ሁለተኛ ጎሉም “የክፍለዘመኑ ምርጥ ጎል” መባሏ አይዘነጋም።
ማራዶና በዚህ ጨዋታ የለበሰው ማሊያ በ8 ነጥብ 93 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል።
ታሪካዊዋ ኳስም በ2 ሚሊየን ፓውንድ በጨረታ መሸጧ አይዘነጋም።
የቀድሞው የናፖሊ እና ቦካ ጁኒየርስ ኮከብ በ60 ዓመቱ በ2020 ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም አርጀንቲናዊውን ኮከብ የሚያወሱ ጉዳዮች አሁንም ድረስ መሰማታቸውን ቀጥለዋል።